ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአፄ ኃይለ ሥላሴ ፎቶ ግራፍ አንሺ በመሆን ያገለገሉት ሰር ሞሂንድራ ዲሎን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ሞሂንድራ በአፄ ኃይለሥላሴ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ላይ አብረዋቸው በመጓዝ ምስሎችን ያስቀሩ እንደነበር በህይወት ድርሳናቸው ላይ ሰፍሯል።
የ85 ዓመቱ ሞሂንድራ የ19 77ቱን የኢትዮጵያ ድርቅ በምስል በማስቀረት ይታወቃሉ። ሞሂንድራ በሙያቸው ስማቸውን የተከለበትና አሻራውን ያኖሩበት ይህ ሥራቸው መሆኑን የሚናገሩ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ረሃቡ በተከሰተበት ገጠራማ አካባቢዎች ለ13 ወራት በመቀመጥ ዕለት በዕለት በረሃብ የተጎዱ ጨቅላ ሕፃናት ዓይናቸው ሥር ሲሞቱ መመልከታቸው በአንድ ወቅት ተናግረዋል።
ሞሂንዲራ ከመሐመድ አሚን ጋር በመሆን የቀረፁትና ‘አፍሪካን ካላቫሪ’ በሚል ርዕስ የሠራው የ30 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረውን ረሃብ ለዓለም ሕዝብ በማሳየት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ይህን ዘጋቢ ፊልም ተከትሎ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ የዓለም ዐቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የተለያዩ እርዳታዎችን በመጫን ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል:: እማሆይ ቴሬሳን የመሰሉ ታላላቅ ሰዎች ፊልሙ ያሳደረባቸውን ስሜት መግለጻቸውም ይታወሳል።
ሞሂንድራ፣ እማሆይ ቴሬሳ እጁን ይዘው ” ልጄ ፈጣሪ ይህንን ፊልም አንድትቀርጸው መርጦሃል” እንዳሉት በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር። ሞሂንድራ ለአፄ ኃይለሥላሴና ለኢትዮጵያ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በልጅ ልጃቸው ዘረያቆብ አስፋወሰን ኃይለስላሴ በኩል “ናይት ኮማንደር” የሚል ዕውቅና ተቀብለዋል።
ራሳቸውን በራሳቸው የፎቶግራፍ ማንሳት ጥበብን ማስተማራቸውን የሚናገሩት ሞሂንድራ ከአጼ ኃይለስላሴ ሌላ የኬኒያ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬኒያታ፣ የኡጋንዳውን ኢዲያምን ዳዳ፣ ሮበርት ሙጋቤ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎችን እንቅስቃሴ በምስል ማስቀረት ችለዋል።
“ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር መስራት በጀመርኩበት ወቅት ” የአፍሪካ መሪ” ተደርገው ይታሰቡ ነበር ” የሚሉት ሰር ሞሂንድራ በወቅቱ ተከስቶ የነበረው ረሃብ የነበራቸውን ሞገስና ተቀባይነት እንደጎዳው በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ ገልጸዋል። ሰር ሞሂንድራ ዲሎን የተወለዱት በሕንድ ፑንጃብ በምትገኝ አነስተኛ መንደር ሲሆን መብራት፣ ንፁህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም መፀዳጃ በሌለበት ቤት ውስጥ ልጅነታቸውን እንዳሳለፉ ይነገራል።