ሰዉ ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል። ግን በስጋዉ፣ በአጥንቱ ወይም በደሙ ምክንያት አይደለም። የስብዕና ወሳኝ አስተሳሰብ ነዉ። መልከም አስተሳሰብ ያለዉ ሰዉ ስለፍቅር፣ ስለእርቅ፣ ስለአንድነት እና ስለሰላም ይመክራል። ከእናት የተሻለ የሰዉ አቃፊ እና ደጋፊ ይሆናል። መጥፎ አስተሳሰብ የተጠናወተዉ ሰዉ ደግም ስለጥላቻ፣ ስለመለያየት እና ስለጦርነት ይሰብካል። ከአዉሬ በላይ ሰዉን ይበላል!
የችግር ትንተና ከተበላሸ መፍትሔዉም ይበላሻል። የሰዉን ስጋ ወይም ደም እንደ ችግር መነሻ ማየት በራሱ ችግር ነዉ። በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች! አንደኛ መጥፎ ሰዎች በሁሉም የአለም ክፍል፣ በሁሉም ፆታ እና በሁሉም ብሔሮች ይገኛሉ። ስለዝህ የታጋቡትን በማፋታት ከመጥፎ ሰዎች መገላገል አይቻልም። ሁለተኛ መጥፎነትን ተፈጥሯዊ ያደርጋል። ሰዉ በደሙ ወይም በስጋዉ ምክንያት መጥፎ ከሆነ ለጥፋቱ ኃላፊነት አይወስድም። ሰውዬዉ አስቦና አቅዶ ራሱን አልሰራዉምና! ተጠያቂዉ ፈጣሪ ሊሆን ነዉ። ችግሩም መፍትሔ አልባ ይሆናል! የሰዉ ችግር አስተሳሰብ መሆኑ ከታመነ ግን በትምህርት ይቀየራል።
ኦፌኮ በደም ጥራት እና በምርጥ ስጋ ችግር ሊፈታ ይፈልጋል። “ዲቃላ”ን ማጥፋት የፕሮግራሙ አካል ማድረጉን በይፋ ተናግሯል። ተጨማሪ “ዲቃላ” እንዳይወለድ በብሔር ተለያይተዉ የተጋቡትን ማፋታት እንደመፍትሔ ይዟል! ይህ ለኢትዮጵያዊያን ምን ማለት ነዉ? ጠቃሚ ባይሆንም ባልና ሚስት በፊቺ ሊለያዩ ይችላሉ። ከአብራካቸዉ የተወለዱ ልጆችስ ምን ይሆናሉ? እጅግ አደገኛ አመለካከት ነዉ! የዘመናችን ታላቁ ትንሽነት ሊባል ይችላል። አንድ ነገር ግን በግልፅ ሊሰመርበት ይገባል። ይህ ድንክዬ እና ጠማማ ኋላቀር አመለካከት ታላቁን እና አቃፊዉን የኦሮሞ ህዝብ ፈፅሞ አይመለከትም።
በየትኛዉም አለም ሰዉን መጥፎ የሚያደርገዉ ብልሹ አስተሳሰብ ነዉ። መፍትሔዉ መጥፎ አመለካከትን ወደ መልካም መቀየር ነዉ። ሚዘናዊ መሆን ግን ያስፈልጋል። ችግሩ ወድህ ብቻ አይደለም! እዝያም ቤት እሳት አለ። ለሀገራችን ህሊውና ሲባል ሁሉም ሊታረም ይገባል!