አርበኛው አባቴ ፤
ይህችን ትልቅ ሃገር፤
ሞገስ የሆነላት ፤
በደም መስዋእትነት፤ በጦር ሜዳ ውሎ ጥይት አገልድሞ፤
ነጻነት የሰጠኝ ፤
ያገሩን መከራ ያገሩን ሰቀቀን ጽዋ ተሸክሞ፤
ስለ እሷ እኔ ልቅደም፤
በሚል ቃልኪዳኑ ፤
ይኸው ተቀምጧል ፤
ከደማላት ሃገር ከባንዲራዋ ፊት እግሩ ተኮርትሞ፤
አዳ ምን ዋጋ አለው፤
ባንዳና ሰላቶ ዛሬም ያደማዋል ከነ ክህደቱ በአራት እግሩ ቆሞ።
ይህንን ብሰማ፤
ይህንን ባየው ነው ፤
እንደ አድዋ ዘማች፤
ደግሞ እንደ ጣይቱ፤
መለዮ ለብሼ ፤
ከፊቱ የቆምኩት፤
እጅ እየነሳሁት መሆኔን ላሳየው የአርበኛ ልጅቱ፤
ቆሜ ምዘክረው ፤ ለእግሩ እግር ልሆን ነው የቆምኩት ከፊቱ።
|| ጃኖ መንግስቱ ዘወሎ ||