ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአገራቸውና በሶማሊያ ድንበር አካባቢ ያለውን ውጥረት በተመለከተ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አዲስ አበባ ላይ መወያየታቸውን የኬንያው የደኅንነት ሚኒስትር ገለጹ።
ከሶማሊያና ከኬንያ ጋር ድንበር የምትጋራው ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈውንና ከእስላማዊው ቡድን አል ሻባብ ጋር የሚፋለመውን የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ለመደገፍ ተሠማርቶ ለሚገኘው የአፍሪካ ኅብርት ሠራዊት አዋጥታለች። የደኅንነት ሚኒስትሩ ፍሬድ ማትያንጊ “በድንበር አካባቢ ያሉትን ችግሮች በመቅረፍ የቀጠናውን መረጋጋት ለማጠንከር በአገራቱ መካከል የትብብር መንገድ ለመፈለግ ያቀደ ውይይት” መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።
የደህንነት ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ያደረጉት ውይይት የተካሄደው የሶማሊያ ኃይሎች ከፊል እራስ ገዝ ከሆነችው የሶማሊያዋ ጁባላንድ ግዛት ከመጡ ኃይሎች ጋር በኬንያ ግዛት ውስጥ ከማንዴራ አቅራቢያ ባለ ቦታ ላይ ከተጋጩ ከሳምንት በኋላ ነው።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የኬንያው የደኅንነት ሚኒስትር ፍሬድ ማትያጊ ወደ ሶማሊያ አቅንተው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሒ ፋርማጆ ሞሐመድ ጋር በመገናኘት የድንበር አካባቢ ፀጥታን ለማጠናከር ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን አድርገው ነበር።
ቀደም ሲልም ሶማሊያ ኬንያን በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባች ነው በማለት ከመክሰሷ ባሻገር በድንበር አካባቢም ያለውን መስፋፋት እንድታቆም ማስጠንቀቋ አይዘነጋም። በሁለቱ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ ባላቸው የጋራ የውሃ ድንበር ይገባኛል ውዝግብ ምክንያት ከሻከረ ቆየት ብሏል። ይህም የባሕር ድንበር ይገባኛል ውዝግብ በዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት በመጪው ሰኔ ወር ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል::