በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መገኘቱን መንግሥት ይፋ አደረገ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መገኘቱን መንግሥት ይፋ አደረገ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር ዛሬ መጋቢት 4 ቀን ይፋ አደረገ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አንድ ጃፓናዊ የቫይረሱ ተጠቂ ሆኖ መገኘቱን  አስታውቋል። የቫይረሱ ተጠቂ የ48 ዓመት ጎልማሳ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ  ለመገናኛ ብዙኃን አባላት በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ግለሰቡ የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም በቦትስዋና በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባቱንም አረጋግጠዋል።

አሁን ላይ የቫይረሱ ተጠቂ ከሆነው ግለሰብ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ሃያ አምስት ግለሰቦች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ያመላከተው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ ፤ ዋነኛ የቫይረሱ ተጠቂ የሆነው ጃፓናዊ ግለሰብ “በቦሌ ጨፌ ለይቶ ማከሚያ” ተቋም ተገቢው የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ከመሆኑ በሻገር እስካሁን ባለው ሁኔታ የከፋ የጤና እክል እንዳልገጠመው ጭምር አብራርቷል።

መደናገጥ እና ፍርሃት ከቫይረሱ እኩል አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ የገለጸው ሚኒስትር መ/ቤቱ፤ በዚህ ቫይረስ የሚያዝ አብዛኛው ሰው፣ ቀላል ሕመም ከያዘው በኋላ እንደሚደን፤ ነገር ግን ዕድሜያቸው በገፉ እና ተጨማሪ በሽታ ባላቸው ሰዎች ላይ ሕመሙ የከፋ ሊሆን ይችላል ብሏል።

መንግሥት እና የጤና ሚኒስቴር በሽታው ቻይና ከተገኘበት ወቅት ጀምሮ ቫይረሱ ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገባና ከገባም ጉዳቱን ለመቀነስ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውቋል። ከ

ዚህ ጋር ተያይዞም ሠባት ሚኒስትሮች ያሉበት የኮሮና ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የመከላከል ጥረቱን እየመራ ሲሆን፣ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ አባላት ያሉት የቴክኒካል ግብረ ኃይል ተቋቁሟል። ቫይረሱን ለመከላከልም በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ውስጥ የድንገተኛ ኦፕሬሽን ማዕከል ተቋቁሞ ሃያ አራት ሰዐት እየሠራ ይገኛልም ተብሏል።

በዚህ ቫይረስ ለተጠረጠሩ ግለሰቦች ማቆያ የሚሆኑ የተለዩ የጤና ተቋማት የተዘጋጁ ሲሆን እስከ 600 የሚሆኑ ሰዎችን ለይቶ ማቆየት የሚችሉ ተቋማት ተዘጋጅተዋል። የካ ኮተቤ ሆስፒታል አስፈላጊው የሕክምና መሳሪያዎች እና ባለሙያዎች ተሟልተውለት ዝግጅት ማጠናቀቁም ነው የተገለጸው።

ማኅበረሰቡ የመከላከያ መንገዶችን ችላ ሳይል እና ሳይደናገጥ ተግባር ላይ በማዋል የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ከመቅረቡ ባሻገር ፤ በጉዳዩ ላይ የበለጠ መረጃ ሲያስፈልግ በነጻ የስልክ መስመር 8335 መደወል ይቻላል መባሉን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ላይ ሰምተናል።

LEAVE A REPLY