ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሜቴክ የቀድሞ ከፍተኛ ሓላፊ ላይ በመሠረተው ክስ የኅብረት ማኑፋክቸሪንግ እና ማሽን ግንባታ ኢንዱስትሪ የሠራተኞች ንጽህና መስጫ (ላውንድሪ) አገልግሎት ኢንዱስትሪው በራሱ ማድረግ የሚችለበት አዋጪ ጥናት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም 1ኛ ተከሳሽ የሆነው ሌተናንት ኮሎኔል ተሰማ ሓላፊነቱን ያላግባብ በመጠቀም ጥናቱን ውድቅ እንዳደረገ በክሱ ተገልጿል።
በተጨማሪም ባለቤቱ የሆነችው 3ኛ ተከሳሽ ሌተናል ኮለኔል ዙፋን በርሄ፣ ጓደኛው የሆነችው 2ኛ ተከሳሽ ኬሪያ ዋስእ እና ወንድሟ ባለድርሻ የሆኑበትን “ክሊን ወሽ ኃ.የተ.የግ.ማህበር” የተባለ ድርጅት ለዚሁ ዓላማ ሲባል እንዲቋቋም ማድረጉን፤ መወዳደሪያ ዋጋ ሳያቀርብ፤ ሌሎች ተወዳዳሪዎች ያላገኙትን የመሥሪያ ቦታ፣ መብራትና ውሃ ኢንዱስትሪው እንዲያቀርብለት በማድረግ ክሊን ወሽ ኃ.የተ.የግ.ማ እንዲሠራው ማድረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህን ተከትሎም ከጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም እስከ ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ድረስ ለድርጅቱ ያላግባብ ብር 1,417,785.05 ብር በመክፈል ጥቅም ያገኘና ያስገኘ መሆኑን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃና ምስክር አረጋግጧል፡፡
የክስ መዝገቡ ከተከፈተበት ጊዜ አንስቶ ሌተናንት ኮሎኔል ተሰማ ግደይ እና ኬሪያ ዋስእ በቁጥጥር ሥር ባለመዋላቸው ክሳቸው በሌሉበት ሲታይ ቆይቶ ነበር፡፡ 3ኛ ተከሳሽ የሆኑት ሌተናት ኮለኔል ዙፋን በርሄ ላይ የመሰረተውን ክስ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሲያቋርጥ ሁለቱን ተከሳሾች ደግሞ ጉዳዩን የተከታተለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡
በዚህ መሰረት ሌተናት ኮለኔል ተሰማ ግደይ በሌሉበት የ9 አመት ፅኑ እስራት እና የ30 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ የተላለፈባቸው ሲሆን፤ ኬሪያ ዋስእ የተባሉት ተከሳሽ ደግሞ የ9 አመት ፅኑ እስራት እና 50ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተወስኖባቸዋል:: የህወሓት አባል የነበሩትና በሌብነት ተጠርጥረው በሌሉበት ዘጠኝ ዓመት የተፈረደባቸው ኮለኔል ተሰማ ግደይ ከዘራፊው ቡድን ጋር በመቀሌ የመሸጉ መሆናቸውን ታማኝ ምንጮች ጠቁመዋል።