ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢሕአዴግ ፈራርሶና ከስሞ ወደ ብልፅግና ከተቀየረ በኋላ መንግሥታዊ መዋቅሮችን ጨምሮ በጸጥታ አካላት ላይ አዳዲስ አደረጃጀቶችን እየተገበረ የሚገኘው የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ፊቱን ወደ መከላከያ አዙሯል:: መከላከያ ውስጥ ሥር ነቀል ማሻሻያዎችን እያካሄደ መሆኑ የሚነገርለት መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ለሚገነባው የመከላከያ ካምፕ ዛሬ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል።
በመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ አማካይነት የሚገነባው የሻለቃ መኖሪያ ካምፑ ፤ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ አዋሽ ቦሌ ቀበሌ የሚገነባ መሆኑን የምዕራብ ሸዋ ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገልጿል።
የመሠረተ ድንጋዩን የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ሓላፊ ሌተናል ጀነራል ጌታቸው ጉዲና፣ ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አምዴ፣ ሜጀር ጀነራል ብርሃኑ በቀለ እና የምእራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ድሪርሳ ዋቁማ አስቀምጠውታል። የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ጌታቸው ጉዲና በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር የሻለቃ መኖሪያ ካምፑ መገንባት ለአካባቢው ልማት፣ ኢኮኖሚ እና ሰላም መስፈን ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።
በ60 ሚሊየን ብር በ12 ሄክታር መሬት ላይ የሚካሄደው የካምፑ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጀመር መሆኑንም አረጋግጠዋል:: የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ድሪርሳ ዋቁማ በበኩላቸው የካምፑ ግንባታ የአካባቢውን ሠላም ከማስጠበቅ በተጨማሪ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አንጻር ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው ፤ የአካባቢው ነዋሪዎችም ይህንን በመረዳት የመጣላቸውን ልማት መንከባከብ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።