ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 በተለምዶ መገናኛ 24 በሚባለው አካባቢ ቤተ ክርስቲያንን ሲጠብቁ ያድሩ በነበሩ ክርስቲያኖችን ላይ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት ሁለት ወጣቶች መሞታቸው፣ በርካቶች መቁሰላቸው፣ ብዙዎችም ለእስራት ተዳርገው መሰንበታቸው የሚታወቅ ነው። ዘግየት ብሎ ሕይወቱ ያለፈው ሦስተኛውን ሰማእት ወጣት ጨምሮ በርካቶች የቆሰሉበት የእምነት ቦታ የቤተክርስቲያን ንብረት መሆኑን ሣይወድ በግድ ያረጋገጠው የታከለ ኡማ መስተዳደር በስተመጨረሻ የይዞታ ማረጋገጫውን ዛሬ ለቤተክርስቲያን አስረክቧል::
በአካባቢው የሚኖሩ ክርስቲያኖችን በጥቂት ቀናት ውስጥ መቃኞ ሠርተው የቅዱስ ገብርኤልንና የቅድስት አርሴማን ታቦት እንዲያስገቡ ያደረጋቸው በአካባቢያቸው ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ መሥሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ከ11 ዓመታት በላይ ለጠየቁት መልስ ጉዳዮ በሚመለከተው የመንግሥት አካል ሳይሰጥ ፓስተር ዮናታን ጥያቄ ባቀረበ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቦታው እንደተሰጠው መስማታቸው እንደነበር አይዘነጋም።
ቦታውን ለፓስተሩ ማን እንደሰጠው በምክትል ከንቲባውና በቋሚ ሲኖዶስ አማካኝነት የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ አጣርቶ የደረሰበትን እንደሚያሳውቅ በመተማመን ሦስቱ ክርስቲያኖች ሰማዕትነትን የተቀበሉበት ቦታ “በጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን መብትና ክብር አስጠባቂ ኅብረት” ከፍተኛ ጥረት ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ እንዲሰጥ መደረጉ ይበል የሚያሰኝ ነው ተብሎለታል::
መንግሥትም የተቀመጡበትን የሥልጣን ወንበር ተገን አድርገው የራሳቸውን ሃይማኖት ለማስፋፋት የሚሠሩ በሥሩ የሚገኙ ባለሥልጣናትን እያጣራ እርምት እንዲወስድ ተደጋጋሚ ግፊት ከጥቃቱ በኋላ መቅረቡና የጸጥታ ኃይሎቹ አሳፋሪ እርምጃ ክፉኛ ያስቆጣው ምዕመናን በማንቂያ ደውል ፕሮግራሞች ወደ አንድነት መምጣቱ የታከለ ኡማ አስተዳደር ሣይወድ በግድ በተለይም ለሁለት ዓመታት ቸል ብሎት የቆየውን ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ እንዲሰጥ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ለቅዱስ ሲኖዶስና ለአዲስ አበባ መስተዳደር ቅርበት ያላቸው የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ ምንጮች አጋልጠዋል::
ከተማ አስተዳደሩ መሬቱን ለቤተ ክርስቲያን እንዲመልስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረገው የጴጥሮሳውያን ኅብረት የመሬቱ ባለይዞታ የሆኑትን የእስልምና እምነት ተከታይ “ቦታው ወንድሞቻችን ሰማዕትነትን የተቀበሉበት በመሆኑ ለመስጊድም ለሌላ አገልግሎትም ቢያውሉት ደስተኛ ስለማይሆኑ ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ይስጡን፤ ለእርስዎ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተነጋግረን ምትክ እናሰጥዎ” የሚል ጥያቄ፤ ” ያሳደግኋቸው ወጣቶች የሞቱበትን ቦታ ለመስጊድ መሥሪያ መስጠት ሐራም ነው። ባለሥልናትም ሆኑ ባለሀብቶች ቦታውን እንዳይወስዱት እንጂ ምትክ ካሰጣችሁኝ ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ውሰዱት” ማለታቸውንም የኢትዮጵያ ነገ ምንጮች ይፋ አድርገዋል::
ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች ክርስቲያኖችን ከሚጠሉ የዘመናችን አክራሪዎች የተለዩ መሆናቸውን የሚያሳየውን ይህን መሰል አኩሪ ተግባር የፈጸሙት የእስልምና እምነት ተከታይ ባለሀብትን ምዕመኑም ሆነ እውነተኛው የሙስሊም ማኅበረሰብ በይፋ ሊያመሰግናቸው እንደሚገባ ለቦታው መመለስ ትልቁን ሚና የተጫወተው የጴጥሮሳውያን ኅብረት ጥሪ አቅርቧል::