ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአዲስ አበባ ከተማ “እንጦጦ” እየተካሄደ ያለውን የእንጦጦ ፕሮጀክት ዛሬ በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጉብኝቱን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ” ከተሞቻችን አንጡራ ሀብት በውስጣቸው ይዘዋል ፤ በእንጦጦ ፕሮጀክት ጉብኝት እንደተመለከትሁት፣ ለውጡ አስደናቂ ነው፣ ሥራው ሲጠናቀቅ ደግሞ አያሌ የቱሪስትና የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል” የሚል ጽሑፍ አስፍረዋል። “ዕምቅ ሀብታችንን ለኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገታችን በጥቅም ላይ ለማዋል አብራችሁኝ እንድትጓዙ እጠይቃለሁ፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬ ነውም” ሲሉም ለአዲስ አበቤ መልዕክት አስተላልፈዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጨማሪም በእንጦጦ መንገድ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችና ባለሱቆች ለመንገድ ማስፋፊያ ሥራው ሲሉ፣ በፈቃደኝነት ኑሯቸውን እና ሥራቸውን ከአካባቢው ስላዛወሩ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ “ለልማት የቀረበውን ጥሪ ተቀብላችሁ፣ በፈቃደኝነት ለጋራ ብልጽግናችን መንገድ ከፍታችኋል፤ መንግሥትም ይህንን ላደረጉ ነዋሪዎች በማኅበር ተደራጅተው የሚሠሩበትን የተሻለ ቦታ እንደሚያመቻች አረጋግጣለሁ” የሚል ጽሑፍ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ አስነብበዋል።