በኹከት የሰነበቱት ደብረብርሃን፣ አዳማና ዋቻሞ ዮንቨርስቲዎች ተማሪዎችን አስመረቁ

በኹከት የሰነበቱት ደብረብርሃን፣ አዳማና ዋቻሞ ዮንቨርስቲዎች ተማሪዎችን አስመረቁ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአዳማ ጀነራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ፣ ደብረ ታቦርና ዋቻሞ ዩኒቨስቲዎች በተለያየ የሙያ ዘርፍ ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎቻቸውን በዛሬው ዕለት አስመረቁ።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በድህረ ምረቃ በመደበኛ እና በተከታታይ መርሀግብር ያስተማራቸውን 1 ሺህ 223 ተማሪዎቹን ዛሬ አስመርቋል።

ዩኒቨርሲቲው ከአምስት ኮሌጆች በ11 የትምህርት መሰኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎቹን ያስመረቀ ሲሆን፤ ከነዚህ በህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በቅድመ ምረቃ በህክምና ዶክትሬት እና በድህረ ምረቃ በኅብረተሰብ ጤና የትምህርት መስኮች 36 ወንዶች እና 6 ሴቶች በአጠቃላይ 42 ተመራቂዎች እንዳሉበት ነው የተነገረው።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሳይንስና እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፥ የሕክምና ዘርፍ ትልቅ ዕውቀት እና ብዙ ትዕግስት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል:: የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ ተመራቂዎች የተማሩትን ትምህርት የሰዎችን ችግር በመፍታት እንዲሁም በጥናት እና ምርምር እንዲያዳብሩ መክረዋል።

የአዳማ ጀነራል ሆስፒታል እና ሜዲካል ኮሌጅ በሕክምና ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል። ሜዲካል ኮሌጁ ዛሬ 15 ተማሪዎች በዶክትሬት ያስመረቀ ሲሆን 1 ሺ 300 የሚሆኑ ተማሪዎች በምህርት ላይ እንደሚገኙ የኮሌጁ ዲን ድሪባ ደገፋ ተናግረዋል። በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚንስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ተመራቂ የጤና ባለሞያዎች በዘርፉ ያለውን የህክምና ጥራት ችግር ለመቅረፍ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም በዶክትሬት ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 26 ተማሪዎችን እና 33 የሕክምና ዶክተሮችን በዛሬው እለት አስመርቋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አፈወርቅ ካሱ ተመራቂዎቹ ቃለ መሀላ በገቡለት የሕክምና ሥነ-ምግባር በመታገዝ ቅን አገልጋዮች እንዲሆኑ አሳስበዋል። በተግባር በተደገፈው ሀይብሪድ ኢኖቬቲቭ ካሪኩለም የቀሰሙትን የሕክምና ትምህርት የሀገሪቱን ብሎም የዓለምን ህዝብ ስጋት ላይ ከጣሉ ዘመን ወለድ የጤና ችግሮች ኅብረተሰቡን ለመታደግ ተግባራዊ እንዲያደርጉት ተመራቂዎችን አሳስበዋል::

ዛሬ ተማሪዎችን አስመረቅን ያሉት ደብረብርሃን ፣ አዳማእና ዋቻሞ ዮንቨርስቲ ከዓመታዊው የተምህርት መጀመሪያ ጊዜ አንስቶ ብሔር ተኮር ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ተደጋጋሚ ኹከቶች የተነሱባቸው መሆኑን ተከትሎ ለረዥም ጊዜ ሲዘጉና ሲከፈቱ መቆየታቸውን ተከትሎ አሁን ላይ ተማሪዎችን አስመርቀናል ማለታቸው በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ያለው የጥራት ጉዳይ አሁንም ትክክለኛውን መስመር እንዳልያዘ ያሳያል የሚሉ አስተያየቶችን አሰንዝሯል::

LEAVE A REPLY