ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሰ ግለሰብ የኮሮናቫይረስ ምልክት ታይቶበትና ተጠርጥሮ ወደ ለይቶ ማቆያ በአምቡላንስ በሚወሰድበት ጊዜ አምልጦ ወደ ትውልድ መንደሩ በመመለስ ላይ ሳለ፤ በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ በቁጥጥር ስር መዋሉ አይዘነጋም።
ይህን ግለሰብ አስመልክቶ ዛሬ ከሰዓት (ሰኞ) የኢትዮጵያ ኅብረሰተብ ጤና ኢንስቲትዩት ባወጣው መግለጫ ግለሰቡ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ በላቦራቶሪ ምርመራ ተረጋግጧል ሲል አስታውቋል።
ግለሰቡ ከአንድ ወር በፊት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለሥራ ተጉዞ የነበረ ቢሆንም፤ ለአንድ ወር ከቆየ በኋላ በሳዑዲ አረቢያ ፖሊስ ተይዞ ወደ ኢትዮጵያ መላኩን የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌትነት አበባው ገልጸዋል።
ከስደት ተመላሹ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በተደረገለት ምርመራ የኮሮና ቫይረስ ምልክቶች ስለታዩበት በአምቡላንስ ወደ ለይቶ ማቆያ ቦታ ሲወሰድ አምቡላንሱን ሰብሮ በማምለጥ እዚያው አዲስ አበባ ወደሚገኘው የእህቱ ቤት አምርቶ እንደነበረ ኃላፊው ተናግረዋል።
ከዚህ በኋላ የአካባቢው ባለስልጣናት ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ ወደ አካባቢው የሚመጡ መኪኖች ላይ ፍተሻ በማድረግ ግለሰቡን ለማግኘት ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል። የግለሰቡን ወንድም አብሯቸው እንዲሆን በማድረግ በመኪና ከሚጓዙ መንገደኞች መካከል ተፈላጊውን ለመለየት ጥረት ማድረጋቸውን የጠቆሙት ሓላፊው ትናንት [ዕሁድ] ጠዋት 5 የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን ከፈተሹ በኋላ ስድስተኛው ላይ ተጠርጣሪው መገኘቱን ይፋ አድርገዋል። ከተፈላጊው ግለሰብ ጋርም ከአዲስ አበባ ጀምሮ ወደ ትውልድ መንደሩ ለማድረስ የተጓዘው የእህቱ ባልም አብሮት መገኘቱን ታውቋል።
ክስተቱን የበለጠ ውስብስብ ለማድረግም ከአዲስ አበባ ቀጥታ ወደ ሚፈልገው ቦታ የሚያደርሰው ትራንስፖርት ከመያዝ ይልቅ በተለያዩ ከተሞች ላይ እየወረደ መጓጓዣውን ሲቀይር ነበር። በዚህም መሰረት ከክትትሉ ለማምለጥ በሚልም ኮምቦልቻ፣ ደሴና ጉጉፍቱ የሚባሉ ከተሞች ላይ ወርዶ መኪና መቀየሩንና መጨረሻ ላይም ጉጉፍቱ ላይ በሳይንት መኪና ሲጓዝ ለጋምቦ ላይ መያዙን ኃላፊው አረጋግጠዋል።
ግለሰቡና አብሮት የነበረው የእህቱ ባለቤት በትራንስፖርት አብረዋቸው ከተጓዙት ሰዎች ባሻገር ከሌሎች ጋር እንዳይገናኙ በማድረግ በለይቶ ማቆያ ውስጥ በመሆን ምርመራና ክትትል ወደሚያገኙበት ወደ አዲስ አበባ ክትትሉ ሲያደርጉ በነበሩት የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ታጅበው እንዲሄዱ ተደርጓል።
ግለሰቡ ተሳፍሮበት በነበረው ውስጥ የነበሩት ወደ 60 የሚደርሱ ሰዎች ምርመራ ተደርጎ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ድንኳን ተዘጋጅቶ ለብቻቸው እንዲቆዩ እንደሚደረግም አቶ ጌትነት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ከተሳፈረባቸው መኪኖች ላይ አብረውት የተጓዙትን መንገደኞች ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፤ የግለሰቡ የምርመራ ውጤት ቀጣይ መወሰድ ያለበትን እርምጃ የሚወስን መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል።