‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አደረገ ›› ማለት … || አሌክስ አብርሃም

‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አደረገ ›› ማለት … || አሌክስ አብርሃም

ሃያል አገር የለም ሃያል አምላክ እንጅ

ኢየሱስ ከሞት በላይ ነገሰ የሚለውን የድል ወንጌል ብዙ ጊዜ ሰምቸዋለሁ እንደዛሬ ግን ገዝፎብኝ አያውቅም! የሰሞኑን በሽታ ፈርቸ ሳይሆን ተገርሜ እያሰብኩ ነው! ከዋልኩበት ውየ ወደቤቴ ስመለስ ስንትና ስንት ርቀት ስነዳ እንዲህ በእረፍት ቀን ለወትሮው የሚርመሰመሰው እግረኛም ይሁን ባለመኪና ፈረንጅና ከመላው አለም የመጣ ህዝብ ለምልክት እንኳን የለም!! ውሻው ሰው የሚርመሰመስባቸው መናፈሻዎች …ወፍ እንኳን ዝር የማይልባቸው ኦና ሁነዋል ጭርር! …ሞት እንዴት አስፈሪ ነገር ነው እናተ? አቤት አለም ሞትን ፍራቻ እንዴት እንደተርበተበተ! ሳይንስ አላዳነው የጦር ሃይል አላዳነው ፍልስፍና አላዳነው ፉከራ አላዳነው በቃ ምንም! ሞት በአይን በማይታይ ቫይረስም ተመስሎ ይምጣ በመሬት መንቀጥቀጥና ጎርፍ…. ብቻ አለም ሚስኪን የሰው ልጅ መጠጊያ የለሽ ፍጡር ነው!

እነዛ በየሚዲያው የሚንጎማለሉ ሃያላን እንደአይጥ ጉድጓዳቸው ውስጥ ተደበቁ፣ እነዛ ውብ ሰውነታቸውን በማራቆት አለምን በቁንጅናቸው ጉልበት የሚያማልሉ ቆነጃጅቶች ዛሬ እንኳን ሰውነታቸውን ራሳቸው መተንፈስ እስኪሳናቸው አፋቸውን ሁሉ አፍነው በፍርሃት ተደበቁ …እነዛ የደፈሯቸውን ምድርን በሚገለባብጥ ቦንብ እና ሚሳኤል የሚያናውጡ ጦረኞች መሳሪያቸውን ወርውረው ሳሙናና ሳኒታይዘርን አድነን አሉ …. ያውምኮ ይሄ የስጋ ሞት ሚጢጢው ሞት ነው

….በሰው ልጅ ታሪክ ብቸኛው ሞትን ድል አድራጊ ኢየሱስ ክርስቶስ ያውም የዘላለም ሞት የሚባለውን በምድርም በሰማይም ገዝፎ የነበረውን ሞት በሃያልና ጨዋ ክንዱ ለዘላለም የደቆሰውና ምናለው… ????

‹‹ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?››

ሃያል አይደለችም ስለተባለችው አገሬ ጭንቀት እሰማለሁ… ሃያል ነኝ ያለችውን አገርም ጭንቀት አያለሁ …ሁሉም በሞት ፊት ያው ነው …ሃያል አገር የለም ሃያል አምላክ እንጅ!!

LEAVE A REPLY