ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ለወራት ተቋርጦ የቆየው የቴሌኮም አገልግሎት ከኮሮና ቫይረስ ክስተት ጋር በተያያዘ እንዲከፈት እየቀረበ ባለው ጥያቄ ዙሪያ እስካሁን የተለየ ነገር እንደሌለ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጹ።
ይህንን በተመለከተ የወረርሽኙ አሳሳቢነት ከታወቀና በኢትዮጵያ ውስጥም የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ከተሰማ በኋላ በተለይ ምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ አካባቢዎች የስልክና የኢንተርኔት አገልገሎቶች መቋረጣቸው፤ ስለበሽታው ያለውን የመረጃ ተዳራሽነት ያስተጓጉላል በሚል ጥያቄዎች በመቅረብ ላይ ናቸው።
በአዲስ አበባ ተጨማሪ ሦስት የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውና በርካታ በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች መኖራቸውን በጤና ሚኒስቴር መገለፁን ተከትሎ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎቶችን የመመለስ ሐሳብ ካለ በሚል ቢቢሲ ለኢትዮቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። ትናንት አመሻሽ ላይ ለሥራ ጉዳይ ከከተማ ርቅው ቆይተው እየተመለሱ መሆናቸውን የገለሱት ሥራ አስፈጻሚዋ ተቋርጦ ስላለው የቴሌኮም አገልግሎት አዲስ መረጃ አንደሌላቸው ነው ምላሽ የሰጡት።
“እንደሚታወቀው ቀደም ብሎ አገልግሎቱ የተዘጋው በዚህ ምክንያት አይደለም። ስለዚህ የተለየ የወሰድነው እርምጃ የለም፤ የተለየ ነገር ካለ እናሳውቃለችኋለን” ሲሉ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ የኢንተርኔቱ መቋረጥ ከፀጥታ ጋር እንደሚገናኝ፤ በመሆኑም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያየተው የሚወሰን ነገር ካለ ይፋ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል። የኢንተርኔት መቋረጡ “በትክክል ለምን እንደሆነ እኛም ሌሎችም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማብራሪያ የሰጡበት ነው” ሲሉም አክለዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት ስልክና ኢንተርኔትን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ስለበሽታው የሚተላለፉ መረጃዎች ኅብረተሰቡ እራሱን እንዲጠብቅ ስለሚያስችለው አገልግሎቱ እንዲከፈት አንዳንድ ሰዎች በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ጥሪ እያቀረቡ ናቸው።