የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ ስያሜው የኢትዮጵያዊያን ነው። ከአቶ ተፈራ ደግፌ 1956 ዓ.ም. እስከ አቶ በቃሉ ዘለቀ 2010 ዓ.ም. በትውልድ ቅብብሎሽ ዘር ሳይለይ፣ ጎሳ ሳይመርጥ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ሆኖ የዘለቀ አንጋፋ ባንክ።
አቶ ተፈራ ደግፌ መጋቢት 12 ቀን 1956 ዓ.ም. ባንኩን ከመረከባቸው በፊት፣ ባንኩ ለኢትዮጵያዊያንና ለአገራችን እምብዛም ግድ በማይሰጣቸው ለራሳቸው ጥቅምና የኢኮኖሚ ዕድገት በሚታትሩ የውጭ አገር ዜጎች ይመራ ነበር። ህንዳዊያን፣ አርመኖች፣ ግብፆችና አውሮፓዊያን አቶ ተፈራ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ባንኩን የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በሚል ስያሜ ያስተዳድሩ የነበሩ ናቸው።
ይህን የተረዱት አፄ ኃይለ ሥላሴ ጣሊያን አገራችንን ከለቀቀ በኋላ ኢትዮጵያዊያን የባንክ፣ የኢንሹራንስና የሕግ ዕውቀቶችን እንዲያዳብሩ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገሮች፣ አሜሪካና ካናዳ ልከው ማሠልጠን ጀመሩ።
ከእነዚህ በየዘርፉ የዳበረ ዕውቀት አዳብረው ወደ አገር ቤት ከተመለሱት ኢትዮጵያዊያን መካከልም ባንኩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባንክነት ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክነት ከተለወጠ በኋላ፣ ባንኩን በኃላፊነት የመሩት አቶ ተፈራ ደግፌ ይገኙበታል።
ከሰሜን ሸዋ አንኮበር አካባቢ ተወልደው ያደጉትና በተለያዩ አጋጣሚዎች የሩሲያ፣ የጣሊያንና የፈረንሣይኛ ቋንቋን የመናገር ክህሎት የነበራቸው አቶ ተፈራ ደግፌ (በኋላም በማታው የብሪቲሽ ካውንስል እንግሊዝኛ ተምረዋል) ባንኩን ከውጭ ዜጎች ጥገኝነት አላቀው ብቃት ባላቸው ኢትዮጵያዊያን ተኩ እንጂ ዘርን፣ ጎሳንና ብሔርን ትኩረት አድርገው ባንኩን ላሳድግ አላሉም።
ከአቶ ተፈራ ደግፌ እስከ አቶ በቃሉ ዘለቀ 1956 እስከ 2010 ዓ.ም. በባንኩ ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞችም ሆኑ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮችም ከሁሉም ብሔር የተውጣጡ ናቸው። የበላይ ፕሬዚዳንትና የባንኩ የቦርድ አመራሮችም እንዲሁ ከአቶ ተፈራ ደግፌ በኋላ ባንኩን በኃላፊነት የመሩት ፕሬዚዳንቶች የመጡበት ወይም የወከሉት አካባቢ ልዩነት፣ ያለፉት ሥርዓቶች በባንኩ ላይ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እንዳልነበረው የሚያመለክቱ ነበሩ።
በየጊዜው የነበሩ የፖለቲካ አመራሮች በባንኩ መሪዎች ላይ ያሳድሩ በነበረው ጫና አመራሮቹ በአቋማቸው ፀንተው ለእስር፣ ለሞትና ለስደት መዳረጋቸውን የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። የቀደሙት የባንኩ ፕሬዚዳንቶች የትውልድ አካባቢ ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው።
ከእነዚህ የባንክ የበላይ አመራሮችም አብዛኞቹ ለእስር የተዳረጉ ነበሩ። አቶ ገዛኸኝ ይልማ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ መስዋዕት ሆነዋል። አቶ ለይኩን ብርሃኑ፣ አቶ ዓለሙ አበራና አቶ ጥላሁን ዓባይ በሥራቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገው መከራ አሳልፈዋል። አቶ አቤ ሳኖ በጊዜው ከነበሩ የፖለቲካ አመራሮች ጋር ባለመስማማት ሥራቸውን ለቀዋል።
እንግዲህ እንደዚህ ነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበርካቶች መስዋዕትነት፣ በበርካቶች እስርና እንግልት አስቸጋሪ ጊዜያትን በማሳለፍ አሁን ለደረሰበት ደረጃም የደረሰው።
አቶ ባጫ ጊና ከመጡ በኋላ ግን በፈጣን ዕድገት ላይ የነበረው ንግድ ባንክ በጥሩ ሁኔታ የቁልቁለት ጉዞውን ተያይዞት ከርሟል። ለዚህ ደግሞ ባንኩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዕቅዱና ከመጣበት ጊዜ አንፃር በሁሉም መስክ ያስመዘገባቸው ውጤቶች ዓይነተኛ ማሳያዎች ናቸው። በሀብት ማሰባሰብ፣ በሠራተኞችና በደንበኞች እርካታ፣ በሠራተኞች ፍልሰት፣ በብድር አቅርቦት፣ እንዲሁም የተበላሹ ብድሮች በመልካም ስምና ዝናው ላይ ያስመዘገበው ደካማ ውጤት ለዚህ አብነቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገር ነው። በውስጡ እስከ 50 ሺሕ የሚደርሱ ሠራተኞችን ያቀፈ ለግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶችም ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ ነበር። በዘርፉ የላቀና የዳበረ ዕውቀት ያላቸው የሠለጠነ የሰው ኃይል የያዘም ጭምር ነበር።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን ከ65 የሚበልጡ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆችና በጣም ብዙ ሠራተኞች ለቀዋል። ከግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክቶች ይልቅ ለአቶ ባጫ ቅርብ ለሆኑ ግለሰቦችና አካባቢዎች የብድር አቅርቦት የሚያደርግ ባንክ እየሆነ መጥቷል። ባንኩ በበርካቶች መስዋዕትነት እዚህ መድረሱንም ረስተው፣ ቁልፍና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ቦታዎች ከአንድ አካባቢ የመጡ ሰዎችን ሲሰገስጉ ከርመዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሁለት ዓመት በፊት የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ተደርገው የተሾሙት አቶ ባጫ ጊና፣ በቅድሚያ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላትን ከኃላፊነት በማንሳት ነበር ሥራ የጀመሩት።
አሁን በረጅም ጊዜ እየተገበሩት ያለውን የባንኩን የተማረ ከፍተኛ የሰው ኃይል የማፈናቀል ዕርምጃ በጥናት ተመሥርቶ ተግባራዊ ለማድረግም፣ በቅድሚያ በቀጭን ደብዳቤ ያነሱት የሰው ኃይል አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰይፉ ቦጋለን ነበር።
ከእሱ በመቀጠል የብድር ክፍል ኃላፊው አቶ ዓባይ መሐሪን፣ የደንበኞች አካውንትና ትራንዛክሽን ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁን፣ የፋይናንስ ኃላፊው አቶ አታክልቲ ኪዳነ ማርያምን፣ የፋሲሊቲ ማኔጅመንት ኃላፊዋ ወ/ሮ መሠረት አስፋውን፣ የብድር ፕሮትፎሊዮ ማኔጅመንት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወንዳለ በላቸውን፣ የንግድ አገልግሎት ትሬድ ሰርቪስ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መሐመድ ኑረዲን፣ ቺፍ ኢንተርናሽናል ኦዲት አቶ ሰሎሞን አለነ፣ የኦፊስ ኦፍ ስትራቴጂ ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሶስና መንገሻን በውድም በግድም ከባንኩ እንዲለቁ ተደርገዋል።
ቀደም ሲል በባንኩ የፕሮሰስ ካውንስል አባል ከነበሩት አሥራ አራት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ የሚገኙት ሁለት ብቻ ናቸው። ለበርካታ ሠራተኞች መልቀቅ ምክንያት የሆኑት ቀደም ሲል የሕወሓት አሁን ደግሞ ለአዲሶቹ ተላላኪ የሆኑ ሁለት ግለሰቦች ናቸው።
ከሰሞኑ ቀደም ሲል የኢንፎርሜሽን ሲስተም ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትና በኋላም የባንኩ የፋይናንስ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት በባንኩ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት ወ/ሮ መሊካ በድሪም፣ እየሆነ ባለው ነገር ባለመስማማት በራሳቸው ፈቃድ ጡረታቸውን አስከብረው መውጣታቸውን ሰምተናል።
ሌላም አለ። በባንኩ ውስጥ ለረዥም ጊዜ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ የባንኩ የግዥ ክፍል ምክትል ፕሬዚዳንት ተደርገው የነበረ ቢሆንም፣ በከፍተኛ ኃላፊነት ካሉት አመራሮች ጋር ከግዥ ፕሮሲጀር ጋር ባላቸው ቅራኔ አሁን በቀጭን ትዕዛዝ የግዳጅ ዕረፍት እንዲወጡ ተደርገዋል።
በተለያዩ የሥራ ክፍሎች በመሥራት የባንኩን አሠራር ጠንቅቀው የሚያውቁት አቶ ኤፍሬም፣ በሥራ የማይታሙና በሥራቸው ፍፁም ጠንቃቃና ጠንካራ ሠራተኛ እንደነበሩ ይነገራል። በፋሲሊቲ ወይም ግዥ ክፍል ያለውን ኔትወርክ በመቆጣጠር የግዥ ሒደቱን በሚፈለገው መንገድ ለመዘወር ይረዳ ዘንድም፣ በእሳቸው ሥር የነበሩ አራት ዳይሬክተሮች አብረው የግዳጅ ዕረፍት ተሰጥቷቸዋል።
ይህ መጠነ ሰፊ የሰው ኃይል ማፈናቀል የባንኩን ሠራተኞች የሥራ ተነሳሽነትና ሞራል የገደለ ከመሆኑም በላይ፣ በአጠቃላይ የባንኩ የሥራ እንቅስቃሴና ትርፋማነት ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ይገመታል። አቶ ባጫ ባንኩን በራሳቸው ሰዎች አሲይዘዋል ስንልም በማስረጃ ነው።
በቀጥታ ትዕዛዝ ያለ ምንም ውድድርና የውጭ ማስታወቂያ ሳይወጣ ከሌሎች ባንኮች ተዛውረው የተቀላቀሉ የመካከለኛ አመራሮች አሉ። በተራ ሠራተኝነት በየክፍሉ የተሰገሰጉትን ቤት ይቁጠረው። ደግሞ እኮ የመጡት እነዚህ ሠራተኞች የተሻለ አቅምና ችሎታ ቢኖራቸው እንኳ ባልከፋ። ችሎታቸው፣ ብሔራቸውና ቋንቋቸው፣ እንዲሁም የከፍተኛ አመራሮች የቅርብ ወዳጅ መሆናቸው ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበርካታ የባንኩ ቀደምት ትጉህ ሠራተኞች እዚህ የደረሰ ነው። ይሁንና የአንድ ብሔር የበላይነትን በዚህ ደረጃ ለማስፈን የሚደረገው ይህ ሩጫ ግን፣ ባንኩን ብቻ ሳይሆን የአገርን ኢኮኖሚ የሚጎዳ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
አሁን የባንኩ የተቀማጭ ሒሳብ ከመቸውም ጊዜ በላይ እያሽቆለቆለ ነው። ከባንኩ የወጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ባንኩ በከፍተኛ ሁኔታ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰባቸው ከመሆናቸውም በላይ፣ በየሄዱበት ቦታ ሁሉ ደንበኞቻቸውን ይዘው ሲጓዙ ከርመዋል።
ይህ ደግሞ ለአገራዊ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የፋይናንስ ምንጭ ለሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የተለመዱ ግዙፍ አገራዊ ሥራዎቹን በስፋት አጠናክሮ ለመቀጠል አዳጋች እየሆነበት እንደሆነ ይሰማል።
ከአቶ ባጫ ጀርባ አይዞህ በርታ ባይ ወገን እንዳለ ይሰማኛል። ይህ ባይሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ችግር ሲፈጠር በፍጥነትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስቆም ይቻል ነበር። ባንኩ የሌላ አገር ባንክ ይመስል ችግር እንዳለበት እየታወቀ ባልሰማ ማለፍም፣ ነገ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ለሚመጣው ጫና አለመጨነቅ ነው።
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ይህንን ጽሑፍ ካዘጋጀ በኋላ አቶ አቤ ሳኖ የባንኩ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን ሰምተናል። ቢዘገይም ይህ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው። አቶ አቤ ሳኖ በዕውቀታቸው የማይታሙ ባንኩን፣ ሠራተኞቹንና የባንኩን ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ በአቋማቸው የሚታወቁ ጠንካራ መሪ ነበሩ። ይህንኑ ባህሪያቸውን እንደማይለውጡት ተስፋ አለን።
ቀደም ብዬ እንዳልኩት ንግድ ባንክ አገር ነው። የባንኩ ዕድገት የአገር ዕድገት ሲሆን፣ በንግድ ባንክ ላይ የሚመጣ ውድቀት ለአገር ውድቀት ለኢኮኖሚውም ጫና ነው። ስለሆነም አሁንም አልረፈደም። ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻግር ልምድ፣ በዘርፉ የዳበረ ችሎታና አቅም ያለው ባለቤት ይፈልጋል። አሁን መንግሥት ዓይኑ በርቶ እርስዎን መርጧል። የባንኩ አብዛኛው ሠራተኛም በእርስዎ ተስፋ አድርጓል። ባንኩ በሁለት ዓመት ውስጥ የተፈጸሙ ስህተቶችን ማረምና ወደነበረበት ሁኔታም መመለስ ከእርስዎ የሚጠበቅ የመጀመርያ ተግባር ነው።
አሁን በበርካታ የባንኩ ክፍሎች ድንዛዜ ነግሷል። ሁሉም አፍ አውጥቶ አይናገረው እንጂ ክፍሎቹ የሐዘን ቤት መስለዋል። ይህንን የተዳከመ ሠራተኛ በማነቃቃት ወደ ሥራ መመለስም ለነገ የሚባል ሥራ ሊሆን አይገባውም።
ከተቻለም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አልያም እርስዎ ፕሬዚዳንቱ በሚሊኒየም አዳራሽ ከአጠቃላይ ሠራተኞች ጋር ውይይት በማድረግ ችግሮቹን ነቅሰው ማውጣት ያሻል።
በከፍተኛ ሁኔታ እየተደረገ ያለውን የሰው ኃይል መፈናቀልና ባንኩን በአንድ ብሔር ለመሙላት የሚደረገውን ጥረት ሊያስቆሙ ይገባል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለፈው ስህተት እንዳይደገም መጠንቀቅ ይገባል።
|| gadisanobako@gmail.com ||