ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአዲስ አበባ ወረዳ 6 በተለምዶ ጎፋ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ጋራዥ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ሁለት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጉዳት ሲደርስባቸው፥ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ደግሞ ወድሟል።
የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ፥ የእሳት አደጋው የደረሰው ትናንት ምሽት 2 ሰዓት ከ50 አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል።
የእሳት አደጋው በአንድ ጋራዥ ላይ የደረሰ ሲሆን እሳቱን ለማጥፋት ከተሰማሩት 71 የእሳት አደጋ ሰራተኞች መካከል ሁለቱ ቀላል ጉዳት አጋጥሟቸዋል። በተጨማሪም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም ከ30 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከቃጠሎው ማትረፍ መቻሉንም ሓላፊው ተናግረዋል።
እሳቱን ለመቆጣጠር አምስት ሰአታትን የፈጀ የማጥፋት ስራ የተከናወነ ሲሆን 250 ሺህ ሊትር ውሃ ጥቅም ላይ ውሏል። የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ ነው። የእሳት አደጋውን በመቆጣጠር ሂደት የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸው ተሰምቷል።