የታጋቹ ማስታወሻ || በእውቀቱ ስዩም ከሚሲሲፒ ወንዝ ወዲህ ማዶ

የታጋቹ ማስታወሻ || በእውቀቱ ስዩም ከሚሲሲፒ ወንዝ ወዲህ ማዶ

ዛሬ ከቤት ወጣሁ። የምሰነብትበት ከተማ ኦና ሆኗል:: ለወትሮው ሰው እንደ ቅዳሜ ገበያ የሚተራመስበት መናፈሻ ጭር ብሏል።  አንድ ጥቁር ሽማግሌ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጦ፤ ለሁለት ርግቦች ፍርፋሪ ሲመግብ አየሁት።  ወፎቹ እንደ ሙት ልጆች ሰሞኑን ቀላቢ አጥተው ስለሰነበቱ፤ ፍርፋሪው ከሰውየው መዳፍ እስኪወርድ አላስችል ብሏቸው ወደ ሰውየው ጣቶች እንጣጥ እንጣጥ ይላሉ :: ሽማግሌው ገና ሲያየኝ ፊቱ በደስታ በራ!! ብድግ አለና ተመልሶ ቁጭ አለ፤ አይኑን ክፉኛ ሰው ርቦታል።  ያ ርጉም፤ በፈገግታ ይተላለፋል ያሉኝ ይመስል፤ ለፈገግታው ምላሽ ሳልሰጥ ኮስተር ብየ ጉዞየን ቀጠልኩ::

ትንሽ ተራምጄ የቤቴ መዳረሻ አውራጎዳና ዜብራ ለማቋረጥ ስቃጣ ድንገት ኮቴ ሰማሁ።  አንዲት ፈረንጅ እየሮጠች ከፊትለፊቴ ትመጣለች።  ፊቷ በላብ ታጥቧል! የመሮጥ ልማድ እንዳልነበራት ያስታውቃል:: ያው ሩጫ በሽታ የመከላከል አቅም ይጨምራል ሲባል ሰምታ፤ እያዘጠዘጠች ነው:: ድንገት ስታየኝ መንገድ ቀይራ ስታቋርጥ ፤ ከላይ እየከነፈ የሚመጣ አንቡላንስ ለጥቂት ሳታት:: ቤት ገብታ በድንጋጤ እምትሞት ይመስለኛል:: ነፍስ ይማር!!

ህዝቡ እንደ ኤሊ በየድንጋዩ ገብቷል :: ቤቱ ቁጭ ብሎ ያከማቸውን ሲቀለብ ይውላል :: ሱባኤውን ጨርሶ ሲወጣ ደግሞ ኮሌስትሮሉ አሸቅቦ ስቡ ልቡን ደፍኖት ይሞታል:: ችግሩ ኮሮና አይደለም::ችግሩ ሰው ሆኖ መፈጠር ሳይሆን አይቀርም።  ሰው በዘመኑ ያልተጨነቀበት ጊዜ መች ኖሮ ያውቃል? ንጉስ ኦዲፐስ እንዳለው ጨርሶ አለመወለድ ይሻል ይሆን ? ያገራችን አረሆ:-

“ያኔ ነበር እንጂ ሰው አልሆንም ማለት

አዳምና ሄዋን የተፈጠሩለት::”

ያለችው ይሄ ተገልጦላት ይሆን?
አገር ቤት ስደውል ምሬቴን የሚያጣፍጥ ነገር ሰማሁ ፤ ራስን የመጠበቅ ዘመቻው ቢዘገይም ጥሩ እየተፋፋመ ነው፤ እስካሁን በዚህ ደደብ በሽታ የሞተ ዜጋ የለም፤ ለአጎቴ ልጅ ደወልኩለት ፤ አጅሬ፤ ተጣጥቦ ፈረንጅ ለመደብደብ እየወጣ እንደሆነ ነገረኝ ተናድጄ ወረድኩበት ” ይሄንን ጀብድህን ለግብፅ ጦርነት አቆየው፤ የፈረንጅ በረከት ተካፍለህ ከኖርህ፤ ከመአታቸውም ለመካፈል መዘጋጀት አለብህ! ደሞኮ የፈረንጅ መዳኒት ከፋርማሲህ ላይ ቢቀነስ ዳማካሴህና ሶስት ዙር የቡዳመዳኒትህ ነው እጅህ ላይ የሚቀረው ” ብየ ወቀስኩት!

ጊዜየን የማሳልፈው የክትባት ዜና በመጠበቅና ፊልም በማየት ነው፤ ፊልም ሲሰለቸኝ ተነስቼ እንጎራደዳለሁ፤ ወይም አንጎራጉራለሁ፤ ሳሎኔ ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን፤ ሱፌን ግጥም አድርጌ የተነሳሁትን ፎቶ ባድናቆትና ባዜኔታ እያየሁ ፤

“ ይበላሃላ
ይበላሃላ
አንተንም መሬት የበላሃላ “
እያልሁ አዜማለሁ::

ከዚያ ስልኬ ላይ እጣዳለሁ፤ ቴሌግራም፤ ሜሴንጀር እና ቫይረስ ማለቴ ቫይበር እከፍታለሁ፤ የወዳጆቼ ጥያቄ ምክርና መፅናኛ ይጎርፍልኛል።

“በውቄ ከምልክቶች ውስጥ ጀርባ ማከክ እሚባል ነገር አለ እንዴ?” አለኝ አንዱ ደውሎ፤

“ የለም ! “

“ ተመስጌን ! ዝም ብየ ያለሃሳብ ልከካ?”

“ አዎ! እንደልብህ እከክ ! እከካም!”

“ አንዲቱ ” ትኩስ ነገር ደጋግመህ ጠጣ “ ብላ ምክር ሰደደችልኝ ፤

” ትኩስ ነገር ቫይረሱን ይገድለዋል?”

“ባይገድለውም ያቆስለዋል:: ዝም ብለህ ጠጣ”

ቅድም ደሞ ለወዳጄ ለበየነ ደወልኩለት፤

” ቀኑ እንዴት ያልፍልሃል? ምን ስትሰራ ነው የምትውለው?” አልኩት፤

” ባንድ እጄ ሪሞት ኮንትሮሌን፤ ባንድ እጄ ቆመጤን ይዤ ፤ ሶፋ ላይ ውየ አድራለሁ ‘’ ( ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ቆመጥ በሚለው ቃል ውስጥ የሚገኘው “ለ” በ” መ ‘ ተተክቷል )
“ፊታችሁን አትንኩ መባሉ በጀ እንጂ ፤ ፊታውራሪያችሁን አትንኩ ቢባል አልቆልኝ ነበር:: ሁሌም ከንቅልፌ ስነቃ ፤ እጄ፤ በግራና በቀኝ እግሬ መካከል ድንበር የሚያሰምር ይመስል ጭኔ መሀል ነው እማገኘው” አለና ተከዘ፤

LEAVE A REPLY