ትራምፕ ጉድ አፈሉ :-ብዙናይጄሪይኖች በወባ ኪኒን ታመሙ || ታምሩ ገዳ

ትራምፕ ጉድ አፈሉ :-ብዙናይጄሪይኖች በወባ ኪኒን ታመሙ || ታምሩ ገዳ

እስከ አሁን ድረስ ክትባት እና መድሐኒት ላልተገኘለት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ መፍትሔ ይሆናሉ ተብለው መላ ምት የሚሰጥባቸው ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ መድሐኒቶች ቢበራከቱም የአንዳንዶቹ መድሐኒቶች ጉዳት ወዲያውኑ እየታየ መጥቷል።

የአሜሪካው ፕ/ት ዶናል ትራምፕ በትላንትናው እለት በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ የሰጡት መግለጫ ላይ “ለወባ መድሐኒት የሚውለው ክሎሮኪን ፎስፌት ኪኒን ለኮሮና ቫይረስ መከላከያነት ጥሩ ፍንጭ አሳይቶናል” ማለታቸውን የሰሙ በርካታ የናይጄሪያ ፣ሌጎስ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ በገፍ ወደ መድሐኒት መሸጫ ቤቶች /ፋርማሲዋች/ በመጉረፍ በህክምና ባለሙያዎች ገና እውቅና ያልተሰጠው፣መጠኑ ያልታወቀ ክሎሮኪን ኪኒን “ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ” በማለት በመጠቀም ለሆስፒታል መዳረጋቸውን የሌጎስ ግዛት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ኦሮሊዋ ፊኒህ አስታውቀዋል።

ከናይጄሪያ የወጡ ዘገባዎች እንደገለጹት የአሜሪካው ፕ/ት ትራምፕ ለህዝባቸው “የክሎሮኪን ኪኒን አመርቂ ምልክት አሳይቷል “ማለታቸው ዜናውም በአንዳንድ የዜና አውታሮች እና በበርካታ የናይጄሪያዊያን ማህበራዊ መረቦች አማካኝነት መሰራጨቱ ተከትሎ ለወባ መከላከያ ቀደም ሲል በስምንት ሺህ ሊራ የሚሸጠው ክሎሮኪን ኪኒን ዋጋ በሌጎስ ፋርማሲዎች ውስጥ በቅጽበት ወደ ሀያ አምስት ሺህ ሊራ ማሻቀቡ ተስተውሏል።

አንዳንድ በጭንቀት የተዋጡ ናይጄሪያዊያን ክሎሮኪንን በገፍ መሸመታቸው እና ለክፉ ቀን ብለው ማስቀመጣቸውን ያስተዋሉ የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት” በአሜሪካው የምግብ እና የመድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን (FDA) ጨምሮ በህክምና ባለሙያዎች እውቅና ያለገኘ ኩኒን ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ይሆናል ብላችሁ ሞትን አትጋብዙ፣ከእብደትም ታቀቡ “በማለት በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው።

በአሜሪካው የኦክላሃማ የጤና ምርምር ተቋም ዶ/ር የሆኑት ዶ/ር ጁዲት ጀምስ ክሎሮኪን ፎስፌት በተመለከተ በሰጡት እስተያየት ” ላለፉት ሀምሳ አመታት ማሌሪያን በመቋቋም በውጤታማነቱ የሚታወቀው ክሎሮኪን ወባን(ማሌሪያን) ከሴላችን (cells)ውስጥ እንዳይቆይ ሰለሚያደርገው የኮሮና ቫይረስንም እንዲሁ ሊከላከል ይችላል ብለን እንገምታለን”ብለዋል።

ናይጄሪያ እስከአሁን ድረስ ሶስት በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች የተገኙባት ሲሆን አንደኛው ተገቢው ክትትል ተደርጎለት ያገገመ ሲሆን አሜሪካን፣ ጣሊያን፣ ቻይናን ጨምሮ በሽታው ከከፋባቸው ከአስራ ሶስት አገራት ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ የመግቢያ ቪዛ እገዳ ጥላለች። የኮሮና ቫይረስ እስከ አሁን ድረስ በአለማችን ላይ ከአስራ አንድ ሺህ በላይ ሰዎች ህይወትን የቀጠፈ ሲሆን ከሁለት መቶ ሰባ ሺህ በላይ አጥቅቷል።

LEAVE A REPLY