ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የዓለም ጤና ድርጅት ወጣቶች በኮሮና ቫይረስ ስለሚያዙ ከአዛውንቶች ጋር ያለቸውን ቅርርብ እንዲሁም ከእድሜ አቻዎቻቸው ጋር ያላቸውን ማህበራዊነት ሊያጤኑት እንደሚገባ አስጠነቀቀ።
የድርጅቱ ዳይሬክተር ጄነራል ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በወጣቶች የሚወሰደው እርምጃ ” ለአንዳንዶች የሞትና የህይወት ጉዳይ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።
በዓለማችን ላይ በኮሮናቫይረስ ምክንያት እስካሁን ድረስ 11ሺህ ሰዎች ሲሞቱ 250ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ፣ በበርካታ አገራት በእድሜ ከገፉ ሰዎች ተጋላጭ በመሆናቸው ብቻ በሚሰጡ የጤና ማሳሰቢያዎች ወጣቶች ቸል ማለት እንደታየባቸው ተናግረዋል።
ኮሮና ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት በቻይና የተከሰተ ቢሆንም አሁን ግን በአውሮፓ ስርጭት ተስፋፍቶ ይገኛል።
በጣሊያን በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች በየትኛውም አገር ከሞቱት ሰዎች በላይ ሲሆን፣ አርብ እለት ብቻ 627 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። ይህም በአገሪቱም ሆነ በዓለም ላይ በበሽታው ምክንያት በአንድ ቀን ይህን ያህል ሰው ሲሞት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጄኔቫ ከሚገኘው ቢሯቸው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ” ምንም እንኳ አዛውንቶች ለቫይረሱ ክፉኛ ተጋላጭ ቢሆኑም ወጣቶችም አያመልጡም” ብለዋል።
አክለውም ለወጣቶች መልዕክት አለኝ በማለት ” ቫይረሱ ልትቋቋሙት አትችሉም። ቫይረሱ ለሳምንታት ሆስፒታል ሊያስተኛችሁ ከዚያም ሲያልፍ ልትሞቱ ትችላላችሁ። ባትታመሙ እንኳ ወዴት መንቀሳቀስ እንዳለባችሁ የምትወስኗቸው ውሳኔዎች ለሌሎች የሞትና የሕይወት ጉዳይ ሊሆኑ ይችላሉ” ብለዋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎች በቫይረሱ የሚያዙ መሆናቸውን ነው። ነገር ግን በእድሜ የገፉና ከዚህ ቀደም የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ይበለጥ ተጋላጭ ናቸው ተብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ከሚለው ባሻገር በአካል አለመገናኘት ወይም ራስን ለይቶ ማቆየትን ለመከላከያው አንዱ መንገድ መሆኑን ይመክራል።