በምስሉ ላይ ቁጭ ብሎ የሚታየው፤ ወህኒ አዛዥ ወልደፃድቅ ይባላል፤ ባጤ ምኒልክ ዘመን ከነበሩ ገናና ባለስልጣኖች አንዱ ነበር፤ በዳግማይ ምኒልክ ዘመን የነፋስ በሽታ የሚባል የኮሌራ ወረርሽኝ ተነስቶ ብዙ ሰው ፈጅቶ ነበር፤ በወቅቱ ንጉስ ነገስቱ በሽታው ያልደረሰበት ቦታ በመምረጥ ከአዲስአበባ ወደ አንኮበር ወርደዋል።
በጊዜው በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ግዳጅ ላይ የነበረው ወልደፃድቅ ምኒልክንና ለማግኘት ቀጠሮ ተይዞለት ስለነበር፤ ወደዚያው ጉዞ እንደጀመረ በበሽታው እንደተለከፈ ይረዳል። ወድያው ራሱን ከሰው ነጥሎ ለመቆየት ወሰኖ እንደ ሽፍታ ወደ ዱር ገባ፤
የንጉሱ ዜና መዋእል የሆኑት አለቃ ገብረስላሴ በዘመኑ ፈሊጥ የፃፉትን ብጠቅስ፤
” ወህኒ አዛዥ ወልደፃድቅም በዲቤ ቆላ ጉበላ ክሚባለው አገር ሄዶ ከዱር ገብቶ በዳስ ተቀመጠ:: ነገር ግን ኩላሊት ያጤሰውን ልብ ያመላለሰውን መርምሮ የሚያውቅ አምላክ እኔ ከሞትኩ ለማን ጌታ ይሆናሉ ሳይል ለጌታው ለአፄ ምኒልክ ማሰቡን አይቶ ከሞት አተረፈው”
(ገፅ 150)”
ፈረንጆች “ኮረንቲን” ብለው የሚጠሩትን ነገር በባህላችን እንግዳ ነገር እንዳልነበረ ይህ የወልደፃድቅ ገጠመኝ ምስክር ይመስለኛል። ሰውየው ቤቱ መቀመጥ ሲችል ላካባቢው እንዳይተርፍ በማሰብ፤ ሰው የማይኖርበት እልም ያለ ዱር ውስጥ ገብቶ በዳስ መቀመጡ ይደንቃል።
በሀኪም ሳይመከር፤ በሹም ሳይገደድ፤ በራሱ ፈቃድ፤ በሽታውን ወደ ዋናው መሪ ባስተላልፍ መንግስት ይፈርሳል በሚል ሰጋት ራሱን አግልሉዋል ፤ እና ይህን ሰውየ የመሳሰሉ፤ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የማይሉ ሰዎች እስካሉ ድረስ፤ አገርም ህዝብም ህይወትም እየወደቀ እየተነሳ ይቀጥላል፤