ማርች 2020
አሁን በመላ ዓለም የተከሰተው የኮረና ወረርሽኝ አደጋ ከምንጊዜውም የከፋ ነው። በጥንካሬ፣ በአንድነትና በዲሲፕሊን ከተከላከሉት የሚቋቋሙት መሆኑን ቻይናዎች አሳይተዋል። በቢልዮን ከሚቆጠር ህዝባቸው መካከል የገባውን መቅሰፍት መንጥረው በማውጣት የተቋቋሙት ከሁሉም በላይ ህዝቡ ሆነ መሪዎቹ ዲሲፕሊን ስለአላቸው ነው። ዛሬ እነሆ የስልጣኔ ቁንጮ የሆኑት አውሮፓውያንና አሜሪካኖችን እያስጨነቀ ያለው መቅሰፍት ሊቋቋሙት ፈታኝና ጨካኝ መሆኑን አስመስክሯል።
በአንድ የበለጸገ አገር የጤና ተቋም ውስጥ እንደመስራቴ ካላቸው እውቀት፣ ሃብትና ጠንካራ ድርጅታዊ ቁመና አንጻር የአገሬን ሁኔታ ሳስብ እንቅልፍ ይነሳኛል፣ እንባ ይተናነቀኛል። ከሁሉም በላይ ተማርን ያሉ ፖለቲከኞችንና የዘረኞችን ድንቁርና በየቀኑ ሳይ ተስፋዬ ይሟሽሻል። መገናኛ ብዙሃኑ፣ ሶሻል ሚድያውና ሌላውም ማህበራዊ እንቅስቃሴ ሳይ ምንም አደጋ የሌለ ይመስል ጥላቻውና ወንዝ የማያሻግር፣ ህይወት የማያድን በካይ ፕሮፓጋንዳ ተሞልቶ የማየትን ያህል መራር ነገር የለም። “የጨው ተራራ ሲናድ፤ ሞኝ ይስቃል፣ ብልህ ያለቅሳል” እንዲሉዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ትንሽ ሆኖ መታየት ያዘናጋን ሚሊዮኖች ነን። ጣልያንም ሲጀምራት በጥቂቶች ነበር። ዛሬ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ላይ ናት።
ይታያችሁ! ከአንድ መቶ አስር ሚሊዮን በላይ በድህነትና በዕውቀት ኋላ የቀረው ህብረተሰባችን በሽታው ከተማና ገጠር ከገባ ሲዎችን አይደለም ሚሊዮኖችን ሊገድል እንደሚችል እሙን ነው። በየትኛውም ጊዜ አገራችንን ከገጠሙት የውጭ ወረራዎች ሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ካለቀው ህዝብ በላይ ሊጨርስ ይችላል። ይህን ስል ጨለምተኛነት አጥቅቶኝ አይደለም። የህመሙን አደገኛነትና የህዝቤንም ቸለልተኛነት በማየት ነው።
በተለይ በመርዘኛ የዘር ፖለቲካ የተለከፋችሁና ሰውን እርስ በርስ የምታፋጁ ወገኖች ሆይ! ዘር የማይለይ፣ እናንተንም የማይምር፣ ከእናንተም የከፋ መቅሰፍት መጥቷል። ሰው በመሆናችን ብቻ ሁላችንንም እኩል የሚያጠቃን ጠላት ተጋርጦብናል። ስለሆነም ፖለቲከኞች፣ አክቲቢስቶች፣ ባለሃብቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ ባለስልጣናት፣ ሁላችሁም ህዝብ ከሌለ ምንም አይደላችሁም። ለህዝቡም ለራሳችሁም ስትሉ አገር አድን ዘመቻ ጀምሩ።
በሶሻል ሚድያ በተለያዩ ቅድሚያ ልንሰጣቸው በማይገባን ጉዳዮች ላይ ያተኮራችሁ ሁሉ ስለሰው ዘር መትረፍ፣ በተለይምሳይማር ላስተማረን ምስኪን የኢትዮጵያ ህዝብ ስትሉስልካችሁን፣ ኮምፒዩተራችሁን፣ ሚድያችሁን፣ ጉልበታችሁን ሆነ ጊዜአችሁን ለዚህ የተቀደሰ ሰባዊነት አውሉት።
ይህ የከፋ እልቂት በአገራችን ቢስፋፋ፣ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስ ተጠያቂዎቹ ሁላችን ነን። ይህ ህዝብ በስንት ይቀጣ? እንባውንስ ማን ያብስለት? እርሃቡንስ ማን ያስታግስለት? ሰላሙንስ ማን ይመልስለት? ፈጣሪ የማይረሳው ህዝብ ቢሆንም እኛስ በመከራው ጊዜ ልናሳውቀው፣ ልንደግፈው፣ ልናጽናናው አይገባንም? የመቅሰፍቱን አደገኛነት ሳይሸበር ማሳወቅና የሚከላከልበትን መንገድ ከእኛ የተሻለ ማን ይንገረው?
ቤት ዘግቶ መቀመጥ፣ መታጠብ፣ ጭንብል መልበስ፣ ምግብና ውሃ በቀላሉ ማግኘት በሚቻልባቸው አገሮች ችግሩ ካስጨነቃቸው አገራችን ሲደርስ የሚያስከትለውን እልቂት ቆም ብለን እናስብና እንንቀሳቀስ።
እንደዛሬ አንቲባዮቲክ በቀላሉ በማይገኝበት፣ ትንንሹ ህመም ሁሉ በገነነበት በጨለማው ዘመን ከተስቦና ልዩ ልዩ ወረርሽኝ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ራስን በማግለልና በመራዳዳት ከሞት ተርፈው እኛን ያሳደጉን፣ ያስተማሩን የዛሬ ትውልድ ከነሱ ተሽለን መገኘት ይኖርብናል። አገርን በአንድነት በማቆየት፣ በሽታን ተባብሮ በመመከት ለዚህ አብቅተውናል። የአገር ህልውናና የህዝብ ደህንነት እኛ ላይ ሲደርስ አደጋ ላይ ሊወድቅ አይገባውም።
ከተማ ውስጥ ያለው ህዝብ የተሻለ ግንዛቤ ከመገናኛ ብዙሃን ያገኛል። የገጠሩ ህዝብ ግን ምን ማድረግ እንዳለበት በዘመቻ መልክ ሊቀሰቀስ ያስፈልጋል። በማህበር፣ በለቅሶ፣ በሰርግ፣ በገብያ፣ በእምነት ተቋማት፣ የሚያደርገው መሰባሰብ ለበሽታው መስፋፋት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጾ ለማስገንዘብ ዘመቻ ካልተጀመረ አደጋው የከፋ ይሆናል።
ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ፣ ወ ዘ ተ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሰራተኛ ማህበራት፣ የመንግስት ተቋማት፣ ወ ዘ ተ የመጀመርያ ዘመቻቸው ህዝቡን ስለወረርሽኙ አደገኛነትና መወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ ማሳወቅ ሲሆን በተጓዳኝ አደጋው ቢስፋፋ መደረግ ያለባቸውን የተግባር ቅደም ተከተሎች መንደፍና መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። “እየየም ሲዳላ ነው” እንዲሉ ትኩረታችን ሁሉ ህዝብንና ራስን ማዳን ላይ ይሁን። በዚህ ሰዓት የጥላቻ እሽኮለሌ የሚጫወት ሁሉ የአገርና የህዝብ ብሎም የራሱ ጠላት ነው።
ሰብአዊ አደጋውን በጋራ እንቋቋመው!