የኢንተርኔት እና የኮሮና ግንኙነት ሸኔን የማዳን ባዶ ጩኼት! || ታዬ ደንደአ

የኢንተርኔት እና የኮሮና ግንኙነት ሸኔን የማዳን ባዶ ጩኼት! || ታዬ ደንደአ

ሰሞኑን ከኮሮና ጋር ተያይዘዉ በርካታ ጉዳዮች ይነሳሉ። ትልቁ ጉዳይ የምዕራብ ኦሮሚያ ኢንተርኔት መዘጋት ነዉ። ኢንተርኔት እንዲለቀቅ ጠንካራ ዘመቻ አለ። በዝያ ምክንያት መንግስትን የሚተቹ ድምፆች በርክቷል። ህዝቡ ስለኮሮና መረጃ እንዲያገኝ ለማስቻል ስልክ እና ኢንተርኔት መለቀቅ አለበት ይላሉ። ለህዝቡ ደህንነት ማሰብ ጥሩ ነዉ። ግን በወለጋ ላይ ኮሮናን ለመከላከል የኢንተርኔት ሚና ምን ያህል ይሆናል?

እዉነት ለመናገር መረጃ በጣም አስፈላጊ ነዉ። ኢንተርኔት ባለመኖሩ ህዝቡ የሚያጣቸዉ ተጨባጭ ጥቅሞችም አሉ። መረጃ ለህዝብ ጤና አጠባበቅ ያለዉ ድርሻም ትልቅ መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን ሁሉም ነገር በልኩ መታየት አለበት። ከሚገባዉ በላይ መለጠጥ ችግርን ከመፍታት ይልቅ ችግሩን ያከፈዋል። አንዱን ችግር ለመፍታት ሌላ የከፋ ተጨማሪ ችግር እንዲፈጠር ማድረግ ልክ አይሆንም።

ሁኔታዉን በዝርዝር መመልከት ለሁሉም ይጠቅማል። አንደኛ ወለጋ ላይ ከሸኔ የከፋ ኮሮና የለም። በምክንያት ማሳየት ይቻላል። ሸኔ በወለጋ ላይ ለመናገር የሚቀፍ ወንጀል ሲፈፅም ከርሟል። ብዙ ሰዎችን ያለምክንያት ገሏል። የበርካቶችን ሬሳ አቃጥሏል። ብዙዎችን አካለ ጎደሎ አድርጓል። አከባቢዉን በማቃወስ ሠላም እና ልማት እንዳይኖር አድርጓል። ሴቶችንና ወንዶችን ደፍሮ የዜጎችን ሞራል ሰብሯል። ሰዉ የራሱን ስጋ እንዲበላ አስገድዷል። ሰዉ የሚቃጠልበትን እንጨት ለቅሞ ተሰቅሎ ተቃጥሏል። ሴቶችንና ወንዶችን ጠልፎ ደብዛቸዉን አጥፍቷል። ስለዝህም ወለጋ ላይ ከሸኔ የከፋ አደገኛ ኮሮና የለም ማለት ይቻላል። አንዱን ኮሮና ለመከላከል ለአደገኛዉ ኮሮና መንገድ መክፈት ደግሞ ትክክል አይሆንም!

ሁለተኛ ወለጋ ለኮሮና ተጋላጭ አይደለም። በርካታ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል። ዋናዉ ግን የአከባቢዉ ፀጥታ ነዉ። የአከባቢዉ ፀጥታ ያልተረጋጋ መሆኑን ሁሉም ያዉቃል። ስለሆነም ወደ አከባቢዉ የሚሄድ ቱሪስት ወይም የዉጭ ሀገር ሰዉ አይኖርም። ኮሮና ደግሞ በሰዉ የሚተላለፍ እንጂ ከሰማይ የሚዘንብ ቫይረስ አይደለም። ስለዝህ ኮሮና በወለጋ በአጠቃላይ አስጊ አይደለም።

ሦስተኛ የህዝባችንን ደህንነት መጠበቅ ግዴታችን መሆኑን እናዉቃለን። ለዝያ ደግሞ ሌላ የግንኙነት መስመር እንጠቀማለን። እጅግ አብዘኛዉ ህዝብ በሬድዮና በቴሌቪዥን መረጃ ያገኛል። የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንኳን በወለጋ እንደሀገርም በጣም ጥቂት ነዉ። ስለዝህ ለህዝቡ በቂ መረጃ ለማድረስ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ይበቃል። በተጨማሪ ደግሞ በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በኩል የፊት ለፊት ግንኙነት ይኖራል። ኮሮናን ለመከላከል አስፈላጊዉ ሁሉ ይደረጋል። ይህ ግዴታ ነዉ!

ከሁሉም በላይ የጉዳዩ አቀንቃኞች ለህዝቡ ጉዳይ የላቸዉም። አባት ልጆቹ ፊት በሽፍታ ሲገደል እና ሬሳዉ ሲቃጠል ምንም አልተናገሩም። ወለጋ ላይ ሽፍታ ነግሶ የህዝቡ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ሲቃወስ አልተነፈሱም። ሰዉ ታፍኖ መከራዉን ሲያይ ያሉት ነገር አልነበረም። የህዝቡ አገልጋዮች በአደባባይ ተገለዉ ቀብር ሲከለከሉ ድምፃቸዉ አልተሰማም። ታዲያ ዛሬ የወለጋን ፍቅር ከየት አመጡት? የህዝቡ ችግር ጉዳያቸዉ አለመሆኑን እናዉቃለን! ዘመቻዉ በህዝቡ አሳበዉ ሸኔን የማዳን ህልም ነዉ። በሽምግልና ስም ሞክሮ ያልተሳካዉን በኮሮና ለመፈፀም አስቧል! ግን ፈፅሞ አይቻልም። ትንሹን ኮሮና ለመከላከል ሸኔን የሚያህል እጅግ አደገኛ ኮሮና የሚያድን ሞኝ የለም። ህዝባችንን ከሁለቱም ኮሮናዎች ለማዳን ግን አበክረን እንሰራለን። ለሁሉም ግልፅ ይሁን!

LEAVE A REPLY