ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ባለፈው ቅዳሜ አንድ ግለሰብ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጉዞ ኡጋንዳ ከደረሰ በኋላ የኮሮናቫይረስ ተጠቂ መሆኑ መረጋገጡን ተከትሎ የኡጋንዳ ባለስልጣናት ከግለሰቡ ጋር ንክኪ ነበራቸው ያሏቸውን 84 ሰዎች በማደን ላይ ናቸው።
ከግለሰቡ ጋር አብረው የነበሩት ተጓዦች እንዲመረመሩ ከያሉበት እየተጠሩ ነው።
ባለፈው ቅዳሜ የኡጋንዳ ጤና ሚንስትር ሁሉም ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ናቸው ብለው ነበር።
ይሁን እንጂ ሁሉም ተጓዦች ወደየመዳረሻው እንዲሄዱና በእራሳቸው ፍቃድ እራሳቸውን ለይተው እንዲያቆዩ ነበር የተነገራቸው።
ቢቢሲ ከጤና ሚንስቴር በኩል የተሰጠው መግለጫ ሁሉም በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጓዙ መንገደኞች በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሆኑ በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን እነዚያን ተጓዦች ለማግኘት ባለስልጣናት ጥረት እያደረጉ ነው።
ይህ በእንዲህ አንዳለ በኡጋንዳ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ሕዝባዊ ስብሰባ ተከልክሏል። ከክልከላው በኋላ ሕዝብን ሰብስበዋል የተባሉ ሁለት ቀሳውስት ታስረዋል።
በመዲናዋ ካምፓላ ከታሰሩት አንዱ የሆኑት የካቶሊክ ቄስ ለምዕመኔ የሚተላለፍ ስብከት ለመቅረጽ ከቀረጻ ሙያተኞች ጋር ነው የነበርኩት፤ ሰው አልሰበሰብኩም ቢሉም የአካባቢው የአይን እማኞች ግን በርካታ ሰው ሰብስበው እንደነበር መስክረውባቸዋል።
ኡጋንዳ የመጀመሪያውን የኮሮናቫይረስ ታማሚ ያገኘችው ቅዳሜ ዕለት ነበር።
ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያና ናይጄሪያን ጨምሮ ብዛት ያላቸው የአፍሪካ አገራት የቫይረሱ ታማሚ ዜጎቻቸው ቁጥር እየጨመረ ነው።