በጎንደር በሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርቷል የተባለ ታጣቂ ቡድን እጅ እንዲሰጥ ቀነ...

በጎንደር በሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርቷል የተባለ ታጣቂ ቡድን እጅ እንዲሰጥ ቀነ ግድብ ተሰጠ 

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የጎንደር ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርቷል ያለውን ታጣቂ ቡድን እስከ መጋቢት 20/2012 ዓ.ም ድረስ ትጥቁን ፈትቶ ለመንግሥት እጁን እንዲሰጥ ጥሪ አቀረበ።

የአስተዳደሩ መግለጫ እንደሚለው ይህ ታጣቂ ቡድን ተደራጅቶ በከተማው ይንቀሳቀሳል፣ ኬላ ጥሶ ከከተማ ይወጣል፣ ይገባል፤ ሰው ያግታል፣ ግድያ ይፈፅማል፣ የግለሰብ ቤት ነጥቆ ካምፕ ያደርጋል፣ ከባለሀብት በግዴታ ገንዘብ ይሰበስባል፣ የከተማ መሬት አጥሮ በመያዝ ቤት ይሠራል በማለት አመልክቷል።

ይህም ብቻ ሳይሆን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለ ወንጀለኛ ያስፈታል፣ ከፖሊስ ጣቢያ የጦር መሣሪያ ይዘርፋል ሲል ተፈፀሙ ያላቸውን ሕገወጥ ተግባራትን ዘርዝሯል።

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ አካባቢ በጎንደር ከተማ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንዳደረ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲገለጽ ነበር።   

በተለይ ተኩሱ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና “ፋኖ” በተሰኘው ታጣቂ ቡድን መካከል እንደነበር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተገልጿል።

በወቅቱ የተፈጠረውንና አጠቃላይ ሁኔታና በጎንደር ከተማና በዙሪያዋ የሚስተዋለውን የጸጥታ መደፍረስ አስመልክቶ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ዛሬ [ማክሰኞ] መግለጫ አውጥቷል።

የጎንደር ከተማ ያወጣው መግለጫ እንደሚያትተው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ተኩስ “ሕገ ወጥ” ያላቸው ታጣቂዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ላይ የፈጸሙት ጥቃት ነው ብሏል።

በዚህ ጥቃትም የሰው ሕይወት መጥፋቱንና ጉዳት መድረሱን መግለጫው ጠቅሷል።

መግለጫው እንዳለው “በከተማው ከዋናው ፋኖ ውጪ፣ በሕገ ወጥ መንገድ በቡድን ተደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ቡድን በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራትን እያከናወነ ነው።”

አክሎም “ይህ ቡድን ታጥቆና ተደራጅቶ በከተማው ይንቀሳቀሳል፤ ያለምንም ከልካይ ኬላ ጥሶ ከከተማ ይወጣል፣ ይገባል፤ ሰው ያግታል፣ ግድያ ይፈፅማል፣ ዘር ቆጥሮ የግለሰብ ቤት ነጥቆ ካምፕ ያደርጋል፣ ከባለሀብት በግዴታ ገንዘብ ይሰበስባል፣ የከተማ መሬት አጥሮ በመያዝ ቤት ይሠራል” ሲል የቡድኑን ሕገ ወጥነት በዝርዝር በማስቀመጥ ወንጅሎታል።

እንዲሁም ይህ ቡድን በፖሊስ እጅ ያለ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ እስር ቤት ጥሶ እንደሚያስፈታ፣ ከፖሊስ ጣቢያ የጦር መሣሪያ እንደሚዘርፍ፣ አስከሬን አጅቦ በመምጣት ጎንደር ከተማን በተኩስ እንደሚንጥ፣ በአገልግሎት መስጫዎች ተቋማት ውስጥ በመግባት የተጠቀመበትን አልከፍልም እንደሚልም ጠቅሷል።

የከተማ አስተዳደሩ የሕገ ወጥ ቡድኑን ተግባራት ሲዘረዝር “ታዋቂ ግለሰቦችን በቡድን ተደራጅቶ፣ የቡድን መሳሪያ ጭምር ታጥቆ፣ ያጅባል፣ ታጥቆና ተደራጅቶ የመንግሥት ተቋማትን፣ የፓርቲ ቢሮዎችን ይከብባል፤ ያስፈራራል” በማለት ቡድኑን ከሷል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር በመግለጫው ላይ ቡድኑ ከዚህ ሕገ ወጥ ድርጊቱ ታቅቦ የመንግሥት ተገዳዳሪ ኃይል ሳይሆን ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዲመለስ ጥሪ አቅርቧል።

መግለጫው ላይ እንደተጠቀሰው በታጣቂ ቡድኑ ውስጥ ያሉ አባላት መስፈርቱን የሚያሟሉ ከሆነ ወደ ክልሉ የፀጥታ መዋቅር እንዲካተቱ፣ መተዳደሪያ የሌላቸው በከተማ ብድር፣ መስሪያና መሸጫ ቦታ እንዲያገኙ፣ በኢንቨስትመንትና በእርሻ ለመሠማራት ለሚፈልጉ የእርሻ መሬት እንዲሰጣቸውና በቂ መተዳደሪያ ያላቸው ደግሞ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ የሚሉ የመፍትሔ ሃሳቦች ቀርበዋል።

ይህ “ሕገ ወጥ ታጣቂ ቡድን” በተቀመጡት መፍትሔዎች የማይስማማ ከሆነ ግን መንግሥት ሕግን ለማስከበር እንደሚገደድ የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።

በከተማው ሕጋዊ የመንግሥት አስተዳደር እስካለ ድረስ በሕገ ወጥ መንገድ ታጥቆና ተደራጅቶ ከነፍስ ወከፍ እስከ ቡድን መሳሪያ አንግቦና ካምኘ መስርቶ መኖር እንደማይቻል መግለጫው አመልክቷል።

“የሕዝቡ ሠላም የሚረጋገጥለትም የፀጥታ መዋቅሩ ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት እንጂ በሌላ በማንም ኃይል አይደለም” ያለው መግለጫው “ማንኛውም ቡድን ወይም ግለሰብ በከተማው ውስጥ ታጥቆ እንቅስቃሴ ማድረግ የተከለከለ ነው” ብሏል።

አስተዳደሩ በመግለጫ ላይ በሕገ ወጥ መንገድ የተደራጀው ቡድን እስከ መጋቢት 20/2012 ድረስ በሠላም እጁን ለመንግሥት እንዲሠጥ፣ ይህንን አልፈፅምም የሚል ከሆነ ግን የፀጥታ ኃይሉ እምቢተኛውን ወገን ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቅሶ፣ ለዚህም “ሕዝባችን ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናስተላልፋለን” ብሏል።

የከተማ አስተዳደሩ አክሎም ለከተማው ነዋሪዎች፣ ለክልሉና ለፌደራል ፀጥታ አካላት የከተማዋን ሠላም በማስጠበቅ በኩል ላደረጉትና ለሚያደርጉት አስተዋጸጽኦ አመስግኖ የጎንደር ከተማ ፀጥታ ወደ ቀድሞ ሰላሙ እስኪመለስ ሁሉም የበኩሉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

LEAVE A REPLY