ከማላዊ ወደ ሞዘምቢክ በጭነት መኪና ሲጓጓዙ የነበሩ 64 ኢትዮጵያውያን በመተፋፈን ህይወታቸው አልፏል

ከማላዊ ወደ ሞዘምቢክ በጭነት መኪና ሲጓጓዙ የነበሩ 64 ኢትዮጵያውያን በመተፋፈን ህይወታቸው አልፏል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከማላዊ ወደ ሞዘምቢክ ሲጓዝ በነበረ የጭነት መኪና ውስጥ ቢያንስ 64 ኢትዮጵያዊያን በመተፋፈን ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉን ባለስልጣናት አስታወቁ።

ዛሬ ጠዋት በሞዛምቢክ ምዕራባዊ ግዛት በምትገኘው ቴቴ በተባለችው ክፍለሃገር ውስጥ በተገኘው ተሽከርካሪ ውስጥ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 14 ሰዎች በህይወት ተገኝተዋል።

“የሞዛምቢክ የኢሚግሬሽን አገልግሎት ሰራተኞች የጭነት መኪናውን ሞአትዜ በተባለችው የግዛቲቱ ከተማ ውስጥ አስቁመው ሲፈትሹ ነው ሟቾቹን ያገኙት” ሲሉ የቴቴ ክፍለ ሃገር የጤና ባለስልጣን የሆኑት ካርላ ሞሴ ተናግረዋል።

ባለስልጣኗ እንዳሉት በጭነት መኪናው ላይ የተሳፈሩት ሰዎች ህይወታቸው በምን ምክንያት ሊያልፍ እንደቻለ ምርመራ እየተደረገ ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያዊያኑ ህይወት ያለፈው በአየር ማጣት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።

የሞዛምቢክ ብሔራዊ ኢሚግሬሽን አገልግሎት ቃል አቀባይ የሆኑት አሜሊያ ደሪዬሮ እንደተናገሩት ሟቾቹን ያሳፈረው የጭነት መኪና ሾፌር እንዲቆም ሲጠየቅ ፍላጎት አልነበረውም ብለዋል።

ጨምረውም የኢሚግሬሽን ሰራተኞቹ ከመኪናው ውስጥ ድምጽ በመስማታቸው ስደተኞች በውስጡ ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ እንዳረባቸውና እንዲቆም እንዳረጉ ገልጸዋል።

ይህ የሞዛምቢክ ክፍለ ግዛት ወደ ደቡብ አፍሪካ በሕገ ወጥ መንገድ ስደተኞች በስፋት የሚዘዋወሩበት አንዱ ቦታ መሆኑ ይታወቃል።

በህይወት የተረፉት 14ቱ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንደተደረገላቸው ቃል አቀባይዋ ጨምረው ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY