ኩባ የጸረ ኮሮና ወረርሺኝ ሰራዊቷን ወደ ጣሊያን አዘመተች || ታምሩ ገዳ

ኩባ የጸረ ኮሮና ወረርሺኝ ሰራዊቷን ወደ ጣሊያን አዘመተች || ታምሩ ገዳ

ትንሿ የካሪቢያን አገር፣ነገር ግን በጤና አጠባበቅ ይዞታዋ አደጉ ከሚባሉት የአለማችን አገራት በእጅጉ የመነጠቀችው ኩባ ጣሊያንን ክፉኛ የመታው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ስርጭትን ለመመከት የህክምና ባለሙያዎቿን ወደ ጣሊያን ላከች።

በጣሊያን የሎምባርዴ ግዛት የደረሰው አስከፊ የሰው ልጆች ህይወት መቀጠፍን ተከትሎ በአለም በኢኮነሚያቸው አደጉ ከተባሉት እንዷ ከሆነችው ከጣሊያን መንግስት ለቀረበው አለማቀፋዊ የትብብር ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የመጀመሪያው ዙር የሆነ ሀምሳ ሁለት ጠንካራ የኩባ ዶክተሮች እና ነርሶች ቡድን ከሶስት ሺህ በላይ ዜጎቿን በጥቂት ቀናት ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ወደ ተነጠቀችው ጣሊያን ተጉዘዋል።

ነጭ ጓን አጥልቀው(armies of white robs) ወደ ጣሊያን ያቀኑት ፣በላይቤሪያ ተቀስቅሶ የነበረውን የኢቦላ ወረርሺን ጨምሮ ለስምንት ጊዜያት የዘመቱት ኩባዊው የህክምና ባለሙያው ፣የስድሳ ስምንት አመቱ ዶ/ር ሊዮናርዶ ፌራንዴዝ ሰለጣሊያኑ ጉዞ ሲናገሩ”እንደዚህ አይነት ወረርሺኝ ሲከሰት ሁላችንም እንፈራለን፣ነገር ግን አብዮታዊ ግዴታ ስላለብን ፍርሃታችንን ወደ ጎን አድርገን ግዳጃችንን እንወጣለን።በዚህ ወቅት ለህይወቴ አልፈራም የሚል ሰው ልዩ ፍጡር (ሱፐር ሂሮ )መሆን አለበት፣እኛ ግን አብዮታዊ ዶክተሮች ነን” ብለዋል።

ላለፉት ስድሳ አመታት ከአሜሪካ ኢኮኖሚያዊ ማእቀብ የተጣለባት፣ ኩባ እስከ አሁን ድረስ ሀያ አምስት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ያሏት (አስሩ የውጪ ዜጎች ናቸው)ሲሆን እኩል የጤና አቅርቦት ለሁሉም ዜጋ በሚለው ፖሊሲዋ እና በርካታ የህክምና ባለሙያዎችን በማፍራት፣የተፈጥሮ አደጋዎችን እና የቫይረስ ወረርሺኞችን በመዋጋት ረገድ የምትታወቀው ኩባ ሰሞኑን በሺህ የሚቆጠሩ ዶክተሮች እና የህክምና ባለሙያዎች ወደ እየማህበረሰባቸው በመሄድ ቤት ለቤት በመዘዋወር የኮሮና ወረርሺኝ እንቅስቃሴን መቃኘታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

በህክምናው አለም ቀላል የማይባል ቦታ ያላት ኮሚኒስት ኩባ በኢኮነሚ የፈረጠሙ አገራትን ጭምር ማስገረሟ እና ማሳፈሯ አልቀረም። ለምሳሌ ያህል ኢንተርፌሮን አልፋ-2B(Interferon Alfa-2B)የተባለው ኩባ ሰራሽ የጸረ ኮሮና ቫይረስ መድሐኒት ሰሞኑን በአገሯ ውስጥ እና በቻይና ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን በማከም ደረጃ ጥሩ ውጤት አሳይቷል።

የህክምና ዶክተሮች በነፍስ ወከፍ ስርጭት በተመለከተ ኩባ ከአሜሪካ፣ከቻይና፣ከደ/ኮሪያ፣ከጣሊያን የተሻለች አገር መሆኑዎን የህክምና መረጃዎች ይገልጻሉ።”ለአለማቀፋዊ ችግር አለማቀፋዊ ምላሽ” የሚል ፖሊሲን የምትከተለው ኩባ ሰሞኑን የኮሮና ቫይረስን ለመዋጋት የህክምና ዘማቾቿን ወደ ቻይና፣ደ/ኮሪያ፣ጃማይካ፣ቬንዙዌላ፣ኒኳሯጓ ሱሩናሚ እና ጊሪናዳ በመላክ አለማቀፋዊ አጋርነቷን በተግባር አሳይታለች።

LEAVE A REPLY