የምድራችን ወቅታዊ ፈተና የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከለል እና ለመቆጣጠር ያሉን ጊዜያዊ አማራጮች ማህበራዊ ፈቀቅታን ተግባራዊ ማድረግ፣ በቤት ውስጥ መወሠን እና እጅን በሣሙና ወይም ሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ኬሚካሎች ማፅዳት እንደሆነ ተደጋግሞ እየተነገረን ነው።
የእነዚህ መከላከያ መንገዶች እንደየአጠቃቀማችን ከሞላ ጎደል ውጤታማ መሆናቸውን ከተሞክሮዎች እየታየ ነው። ሆኖም ግን ከቫይረሱ የተላላፊነት ፍጥነት፣ የግብዐቶች አቅርቦት እና ከማህበረሰቦች ታዛዥነት ድክመት እና ሌሎች ምክንያቶች አንፃር ውጤታማነታቸው ዘላቂ እንዳልሆነና በአስተማማኝ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እንደማያስችሉ የተጠቂዎች ቁጥር በየደቂቃው እያሻቀበ መሄድ ማሣያ እየሆነ ነው።
ለቫይረስ መከላከያ አስተማማኝ የሚባለው ክትባትም ከቫይረሱ የሥርጭት ሽምጥጫ አኳያ በጊዜ እንደማይደርስ ተረድተናል። ከነዚህ ውጭ ስርጭቱን በአስተማማኝ እና በፍጥነት ለመግታት የቀረው አማራጭ ምርመራ ነው።
በርካቶችን መመርመር
ምርመራን ከሌሎች አማራጮች የተሻለ የሚያደርገው አብዛኞቹ የቫይረሱ ተጠቂዎች የህመም ምልክት ስለማያሳዩ በርካታ ሰዎችን በአጭር ጊዜ መመርመር ከተቻለ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች በፍጥነት በመለየት በሽታው እንዳይስፋፋ ማድረግ እና ብዙ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠር ያስችለናል።
አሁን በብዙ ሀገራት በስራ ላይ ያለው የ PCR ቴክኖሎጂ የህዋሱን ዘረ መል በመቅዳትና በማራባት የሚሠራ በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀ ላብራቶሪ፣ የመመርመሪያ መሣሪያና ኬሚካሎች እንዲሁም የላቀ ስልጠና የወሠዱ ባለሙያዎች የሚጠይቅ፤ ውጤቱም ቀናት የሚወስድ በመሆኑ እንደልብ በየቦታው በርካቶችን በመመርመር በሚፈለገው ፍጥነት ተጠቂዎችን የመለየት ስራ አዳጋች አድርጎታል።
ይኽ ምንያህል ከባድ እንደሆነ በጤና አጠባበቅ ከአለም ሁለተኛ እንደሆነች በሚነገርላት ጣልያን የበሽታው ስርጭትና የጉዳቱን መጠን በመታዘብ መረዳት ይቻላል።
ነገር ግን አብዛኞችን በዝቅተኛ ደረጃ የጤና ተቋማትና በመሥክ ለመመርመር የሚያስችሉ የምርመራ ቁሶች መፈብረክ ቢቻል የቫይረሱን ስርጭት ባጭር መቅጨት ይቻላል ።
ለመሆኑ እንደሌሎች ቫይረሶች (ሄፓታይትስ፣ ኤች አይ ቪ እና ወዘተ) የላቀ ድርጅት ያለው ላብራቶሪ፣ ውድ ኬሚካሎችና ከፍተኛ ስልጠና ያለው ባለሙያ የማይጠይቁ የመመርመርያ ቁሶች (ኪቶች) መፍጠር ለምን አልተቻለም?
‘የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ (ቀላል ኪቶች) በ24 ሰዐት ውስጥ ማምረት ይቻላል። ታዲያ ለምንድን ነው ሀገራት ምርመራውን (በስፋት) ለመከወን የተቸገሩት?’ በሚል ርዕስ ሲኤንኤን በፌስቡክ ገፁ ባሰፈረው ፅሁፍ
“ተችሎ ነበር” ይለናል። ምን ተፈጠረ?
ኦልፈርት ላንት የተባሉ የጀርመን ተመራማሪ በኮሮና ቫይረስ ዝርያ ለ30 አመታት ጥናት ሲያደርጉ የቆዩ ሳይንቲስት ናቸው።
ተመራማሪው ከዚህ ቀደም ተነስቶ ለነበረው የመተንፈሻ አካል ህመም SARS አምጭ የነበረውን COV-1 ለመለየት የሚያስችል መመርመሪያ ሠርተው ሥለነበር በጃንዋሪ ወር መጀመሪያ ሪፖርት ለተደረገው ለኖቭል (እንግዳ) ኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ፈጣን ኪቶችን ማዘጋጀት ፈለጉ።
ለወትሮው አንድ አዲስ ቫይረስ ሲገኝ መመርመሪያ
ለማዘጋጀት የተህዋሱ የዘረ መል ስንድት በምርምር እስኪጠናቀር መጠበቅ ቢያስፈልግም ኦልፈርት ላንት
ግን ከቫይረሱ ፈጣን ተስፋፊነት አንፃር ይኽንን መጠበቅ አልፈለጉም።
ሶስት አይነት የዘረመል ስንድቶችን(genetic sequencing ) ታሳቢ ያደረጉ ሶስት አይነት ኪቶች አዘጋጅተው ሆንግ ኮንግ ለሚገኝ የሮች ኩባንንያ ላብራቶሪ ላኩ። የተገኘውን ውጤታማነት ላንት “ፍፁም” (perfect) ሲሉ ነበር የገለፁት ።
በጃንዋሪ 17 2020 የአለም ጤና ድርጅት WHO የላንትን የምርመር ውጤት በድረ ገፁ አትሞ የመጀመሪያዉ መመርመሪያ መሆኑን አሳወቀ።
ይሁን እንጂ የሚጠበቁ መመርመሪያውን በስፋት ለማዳረስ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ተቆጠበ።
ሳይንቲስቱ እስከ በፌብርዋሪ ወር መጨረሻ ከ400 ሚሊየን በላይ በላይ መመርመሪያዎችን ማምረት እንደሚቻል ገምተው ነበር። ይሁንና ውጤታማነቱ ከተመሠከረበት ጊዜ ሶስት ወራት ሊሞላው ቢሆንም አሁንም በርካታ ሀገራት ምርመራውን ለማድረግ እየተቸገሩ ነው።
ከጀርመኑ ላንት በተጨማሪ የሆንግ ኮንግ የቫይረስ ተመራማሪዎች እና አሜሪካዊያን በየፊናቸው መመርመሪያ ኪቶችን መፍጠራቸውን አሳውቀው የነበረ ቢሆንም በፍጥነት ስራ ለማስጀመር ግን አልቻሉም።
አሜሪካውያኑ መመርመሪያው እክል ገጥሞታል ከማለት ውጭ ምን አይነት ችግር እንደገጠመው ያሉት ነገር የለም ። እንግዲህ በ24 ሠዐት መመርመሪያ ማምረት እየተቻለ አገራት ለምን ተቸገሩ ለሚለው ጥያቄ መልስ ያሻናል ።
የሴራ ውጥን- ሀሳብ ተንታኞችን (conspiracy theorists ) መላምት ትተን ለዚህ እንደምክንያት የሚቀርበው የሣይንስ የምርምር ውጤቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያጋጥሙ የቢሮክራሲ ትብታቦችና ማብራሪያ ያልተገኘላቸው የፖለቲከኞች ዳተኝነቶች ናቸው ።
ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ የመመርመሪያ መሣሪያዎችን አስገምግሞ ይሁንታ ለማግኘት ወራት የሚወስደውን የምግብና መድኃኒት አስተዳደርን FDA ፈቃድ ይጠይቃል።
ለዚህም ከመቶ በላይ የሚሆኑ ሳይንቲስቶች በፌብርዋሪ 28 ቀን የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያዎችን ሰርቶ ለማቅረብ የአስተዳደሩ ቢሮክራሲ እንቅፋት ሆኖብናል ሲሉ ለኮንግረስ ‘አቤት’ ብለው ነበር። ዘግይቶም ቢሆን የምግብ እና መድኀኒት አስተዳደር መመርመሪያዎቹ ሳይገመገሙ ስራ ላይ እንዲውሉ ፈቅዷል።
በአንፃሩ ደግሞ በወረርሽኙን እየተቆጣጠሩ ካሉት ጥቂት ሀገራት አንዷ የሆነችው ደቡብ ኮሪያ መመርመሪያዎቹን በሣምንታት ውስጥ ዕውቅና ሰጥታ መጠቀሟ ለበሽታው ቁጥጥር እንደረዳት ይታመናል።
የላንትን መመርመሪያዎች ለመጠቀም የደፈሩ እንደ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ያሉ ሀገራትም ውጤት እያገኙበት እንደሆነ ተጠቅሷል።
የጀርመኑ ሳይንቲስት በአገራቸው በጣም ጥቂት የቫይረሱ ተጠቂዎች በነበሩበት የፌብሩዋሪ ወር መጀመሪያ በኦፔራ ዝግጅት ላይ የጤና ሚኒስትሩን ባጋጣሚ አግኝተዋቸው ስለ ቫይረሱ አደገኝነት ቢያስጠነቅቋቸውም፤ የቻይና ብቻ ጉዳይ አድርገው ለህዝቡ እንዳይነግሩ ቢያስገነዝቧቸውም እንደ ማህበራዊ ፈቀቅታ ያሉትን ርምጃዎች ለመውሰድ እንኳ ባለመቻሉ ዛሬ ባገሪቱ ከ 29000 በላይ የታወቁ ተጠቂዎች መኖራቸውን “በቁጭት” ያወሳሉ።
የሆንግ ኮንግ የቫይረስ ጥናት ተመራማሪ የሆኑትና እንደ ጀርመኑ ሣይንቲስት ለቫይረሱ መመርመሪያ ፈጣን ኪት የሠሩት ሊዮ ፑን በተመሣሣይ በብዛት ምርመራዎችን አድርጎ በሽታውን ለመቆጣጠር እንቅፋት የሆኑት አስተዳደራዊ ሳንካዎች መሆናቸውን ያስገነዝባሉ።
ለወረርሽኙ ቁጥጥር የምርመራ ወሣኝነት ከየትኛውም የመከላከያ መንገድ የበለጠ አስተማማኝ ሆኖ ሳለ፤ መመርመሪያዎችን በብዛት እና በፍጥነት ማምረት እየተቻለ ፖለቲከኞች እና ሌሎች ያገባናል ባዮች ከህክምና ሳይንቲስቶች ጋር ተቀናጅቶ መሥራትን በልግመኝነት ወደ ጎን ትተው ወሣኝ ቢሆኑም ብዙ ርቀት የማይወስዱትን የመከላከያ ዘዴዎች የሙጥኝ ማለታቸው አስገራሚ ነው ።
እንደ ዩናይትድ ኪንግደምና እና ዩናይትድስቴትስ ያሉት የኢኮኖሚ አንዳች አገሮች እንኳ ምርመራዎችን በብዛት አለማካሄዳቸው እያስተቻቸው ይገኛል።
ከነርሱ በተሻለ እንደ አይስላንድ ያሉ ትንንሽ አገራትና እንደ ደቡብ ኮሪያ ያሉት ሀገራት በርካቶችን በየአካባቢያቸው በመመርመር በከፍተኛ ሁኔታ በስርጭቱን መቀነስ ችለዋል።
“በምርመራ ብቻ ነው ተጠቂዎችን ካልተጠቁ ለይተን ስርጭቱን መቆጣጠር የምንችለው” ይላሉ ሳይንቲስቱ።
“ለሁሉም አገራት አንድ ቀላል መልዕክት አለኝ” ብለዋል የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ቴድሮስ አድሃኖም
“ምርመራ ፤ ምርመራ ፤ ምርመራ “
እንደማጠቃለያ ፡ –
የፖለቲከኞች ዳተኝነት እና አስተዳደራዊ ቢሮክራሲዎች ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚረዳውን አስተማማኝ መንገድ ላለመጠቀም እንቅፋት መሆናቸው አለምን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል ።
አሁንም ያለፈውን ወደ ኋላ ትተን በፍጥነት ወደ ምርመራ ተደራሽነት ትኩረት ማድረግ ከተቻለ የከፋ ጥፋት ሳያደርስ መቆጣጠር ይቻላል።
እስከዚያው ሁላችንም የሀኪሞችን ምክር በጥብቅ በመከተል ራሳችንን እና ሌሎችን እንጠብቅ።