ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ – አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አሳሳሲቢ በሆነው ኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት የቆንስላ አገልግሎት ክፍሉን ከዛሬ ጀምሮ ዘግቷል።
በትክክል ላልታወቀ ጊዜ የቆንስላ አገልግሎቱን ያቋረጠው ኤምባሲ ከተጠቀሰው ጽ/ቤት ውጪ ያሉት የኤምባሲው የአገልግሎት ክፍሎች ግን መደበኛ ሥራቸውን ይቀጥላሉ ብሏል።
የአሜሪካ ኤምባሲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከቫይረሱ ስርጭት እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ስርጭቱን ለመግታት ከሚያደርገው ጥረት አንጻር ኤምባሲው በጊዜያዊነት የቆንስላ አገልግሎቱን ለማቋረጥ እንዳስገደደው ጠቁሟል።
ኤምባሲው ለአሜሪካውያን ሲሰጥ የቆየውን የፓስፖርት እድሳት፣ ከአገር ውጪ የወሊድ እና የሞት ምዝገባን ጨምሮ ተዛማጅ ጉዳዮችና አገልግሎቶችን በውል ላልታወቀ ጊዜ መስጠት እንዳቆመ ይፋ አድርጓል።