የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን አስመልክቶ ከኢፌድሪ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የተሰጠ መግለጫ

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን አስመልክቶ ከኢፌድሪ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የተሰጠ መግለጫ

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ፣ በአህጉራችን አፍሪካ፣ እንዲሁም በሃገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት የደቀነ ወረርሽኝ ነው። በአሁኑ ወቅት ይህን ወረርሽኝ መግታት እና መከላከል ትልቅ ሃገራዊ የትኩረት አጀንዳ ነው።

የዜጎችን ህይወት እና ጤና፤ የሃገርን ህልውና እና ደህንነት አደጋ ላይ የጣለውን የዚህን ወረርሽኝ ስርጭት ለመመከት የሁላችንም ጥረት እና ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው። እስካሁን በተለያዩ ሃገራት የተከሰተውን የወረርሽኙን ስርጭት፣ እንዲሁም የአለም ጤና ድርጅት እና የሃገራችን የጤና ባለሞያዎች እና ተቋማት የሚያቀርቡዋቸውን ሞያዊ መረጃዎች እና ምክሮች ከግምት በማስገባት መንግስት ወረርሽኙን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወቃል።

ህዝቡ ስለበሽታው መረጃ ኖሮት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዲችል ስለወረርሽኙ ባህሪያት እና መተላለፊያ መንገዶች በየጊዜው ከሚሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የጥንቃቄ እርምጃዎች በየደረጃው እንዲወሰዱ መንግስት ውሳኔ ማስተላለፉ እና መመሪያዎች መሰጠታቸው ይታወሳል።

እነዚህን ውሳኔዎች እና መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ እስካሁን ያለው ሁኔታ በቂ እና አስተማማኝ ነው ለማለት አይቻልም። ይህን ሁኔታ ለመለወጥ አስፈላጊው መረጃ ለህዝቡ እንዲደርስ የሚደረገው ጥረት ተጥናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ነገር ግን ሆን ብለው እና ለህዝብ ደህንነት እጅግ አደገኛ በሆነ መልኩ አግባብነት ባላቸው የመንግስት መዋቅሮች የሚሰጡ መመሪያዎችን እየጣሱ ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት፣ እንዲሁም ሆን ብለው ወረርሽኙን በተመለከተ አደገኛ የሃሰትኛ መረጃ በማሰራጨት ህዝብን በሚያሸብሩ፣ እንዲሁም በዚህ አጋጣሚ አላግባብ የሆነ ትርፍ ለማካበት የአቅርቦት እጥረት የሚፈጥሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ከሕገ – ወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ለማሳሰብ እንወዳለን።

የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር ቁጥር 661/2002 ስለተላላፊ በሽታዎች ዝርዝር ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን፤ይህ አዋጅ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፤ “ማንኛውም ወደ ሀገር የሚገባ ወይም ከሀገር የሚወጣ መንገደኛ ሀገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የጤና አጠባበቅ መስፈርቶች መሠረት… በተላላፊ በሽታ ሲጠረጠር ለምርመራ የመተባበር ግዴታ አለበት”። እንዲሁም “..ወረርሽኝ ካለበት ቦታ የመጣ ሰው ወደ ሀገር አንዳይገባ ሊታገድ ይችላል”፡፡ ይሄው አዋጅ በተጨማሪም “አግባብ ያለው የጤና ባለሙያ በወረርሽኝ ተላላፊ በሽታ የተያዘን ወይም የተጠረጠረን ማንኛውም ሰው ለተወሰነ ጊዜ ተገልሎ እንዲቆይ’’ ማድረግ እንዳለበት፤ በተጨማሪም “በወረርሽኝ ተላላፊ በሽታ የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ለምርመራ፣ ለሕክምና… ፈቃደኛ መሆን” እንዳለበት ተደንግጎዋል። በአዋጁ መሰረት እነዚህን ድንጋጌዎች መጣስ እስከ ስድስት ወር በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል።

ከዚህም በተጨማሪ የኢፌድሪ የወንጀል ሕግ፤በአንቀጽ 514 ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ተለላፊ በሽታን ማስተላለፍን በህግ የሚያስቀጣ ወንጀል አድርጎ ደንግጎዋል። ይህን አንቀጽ በመጣስ የሚፈጽም ወንጀል እስከ አስር አመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ሊያስከትል እንደሚችል ሲሆን በተለይም ተላላፊው በሽታ በወረርሽኝ ወይም በኢፒደሚክ መልክ የተከሰተ ሲሆን፣ እንደነገሩ ክብደት ቅጣቱ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም ሞት ሊያስቀጣ እንደሚችል የወንጀል ሕጉ ያሳያል።

በተጨማሪም የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 830 የህዝብ ጤና እና ጤናማነትን ለመቆጣጠር በሚል ርዕስ ባሉት ደንጋጌዎች እንደተገለጸው፣ በሽታዎችን በተለይም ተላላፊ በሽታዎችንና ወረርሽኝ ስለመከላከል፣ መኖራቸውን ስለማሳወቅ፣ ለመከላከል የሚረዱ ህክምናዎችን ስለማድረግ ወይም ስለመቆጣጠር የወጣን መመሪያ መጣስ እሰከ ሶስት ወር በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ወንጀል ነው።

በተጨማሪም ለህዝብ ጤና አስጊ የሆን አደጋ እንደሚደርስ በማስፈራራት ሆን ብሎ ህዝብን ያሸበረ ከሶስት አመት በማይበልጥ ቅላል እሰራት ወይም እንደነገሩ ክብደት ከሶስት አመት በማይብለት ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 485 ተደንግጎዋል።

የኮርኖ ቫይረስ ስርጭትን አስመልክቶ የሚሰጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ጥቅሙ በቅድሚያ ለራስ፣ ቀጥሎም በዙሪያችን ላሉ ቤተሰቦቻችን፣ ወገኖችን እና ብሎም ለሃገር ነው። ይህን በመገንዘብ፣ ሁላችንም ተገቢውን ጥንቃቄ አቅም በፈቀደ መጠን እንድናደርግ ጥሪያችንን እያቀረብን፣ ነገር ግን ጉልህ በሆነ መልኩ የቅደመ ጥንቃቄ መመሪያዎችን በመጣስ የህዝብን ጤንነት እና የሃገርን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ፤ እንዲሁም የኮሮና ቫይርስ ስጋትን ሰበብ አድርገው ሆን ብሎ ህዝብ የማሸበር ወንጀል በሚፈጽሙ ላይ፣ ከላይ በተጠቀሱት የህግ ድንጋጌዎችና ሌሎች አጋባብነት ያላቸውን ህጎች መሰረት በማድረግ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ በአፋጣኝ ለመውሰድ የምንገደድ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

LEAVE A REPLY