በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ_19) በሽታ የተያዙ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች መገኘታቸውን ለማሳወቅ የተሰጠ መግለጫ
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ሰማንያ ሰባት (87) ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን በቫይረሱ የተያዙ ሶስት (3) ተጨማሪ ሰዎች በመገኘታቸው በአጠቃላይ በሀገራችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አስራ ዘጠኝ (19) ደርሷል፡፡
የመጀመሪያዋ ታማሚ የ26 ዓመት የአዲስ አበባ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ስትሆን መጋቢት 8፣ 2012 ከብራሰልስ ቤልጅየም እንዲሁም መጋቢት 10፣2012 ዓ.ም ወደ ካሜሮን የጉዞ ታሪክ የነበራት ሲሆን ግለሰቧ የበሽታው ምልክት ስለታየባት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሪፖርት ባደረገው የላብራቶሪ ምርመራ በመጋቢት 19፣2012 ዓ.ም በቫይረሱ መያዟ ተረጋግጧል፡፡
ሁለተኛ እና ሶስተኛ ታማሚዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የ14 እና የ48 ዓመት የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ የበሽታው ምልክት ባያሳዩም ከዚህ በፊት በቫይረሱ ከተያዘ ግለሰብ ጋር የቅርብ ንክኪ ስለነበራቸው በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው የነበረ ሲሆን ግለሰቦቹ በመጋቢት 19፣2020 ዓ.ም በተደረገላቸው የላቦራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በለይቶ ህክምና እየተደረገላቸው ያሉ አስራ ስድስት (16) ታማሚዎች ሲኖሩ አንድ ታማሚ በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላት ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ሁለቱ ታማሚዎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን አንዱ ታማሚ አገግሞ ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገለት ይገኛል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ማግኘት ይቻላል፡
ምንጭ ፡ – የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና አገልግሎት