ለይቶ መቆያ የገቡ ሰዎች ጉቦ እየሰጡ ወደ ከተማ መግባት አሳሰቢ ሆኗል

ለይቶ መቆያ የገቡ ሰዎች ጉቦ እየሰጡ ወደ ከተማ መግባት አሳሰቢ ሆኗል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያልፉ ማንናቸውም መንገደኞች ለ14 ቀናት ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ መወሰኑ ይታወቃል።

በቆይታቸውም መንገደኞች ወጪያቸውን ራሳቸው እንዲሸፍኑ፤ መሸፈን ለማይችሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጪያቸውን እንደሚሸፍን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት የተለያዩ ሆቴሎችና ተቋማት ተዘጋጅተዋል።

ይሁን እንጅ ከሰሞኑ በለይቶ ማቆያ ያሉ ሰዎች ‘ለተቆጣጣሪዎች ጉቦ በመስጠት ወደ ከተማ እየወጡ ነው’ የሚሉ ወሬዎች እየተሰሙ ነው። ለእኛም በማቆያ ቦታው ያለው ሁኔታ ያሳሰበው ግለሰብ፤ ከቦታው ወጥቶ እንደነበርና አሁን መመለሱን ስሙ እንዳይጠቀስ ጠይቆ ነግሮናል።

ይህንኑ ጉዳይ ያነሳንላቸው በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የዓለም ጤና ደንብ ተጠሪ ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ “ይህን በተመለከተ እስካሁን ያገኘነው መረጃ የለም” ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች የወጡ መረጃዎችን ለማጣራት በተደረገው ሙከራም፤ ወጥተው የተገኙት አስገዳጁ የለይቶ ማቆየት ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት፤ በቤታቸው ሆነው ክትትል የሚደረግላቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ዛሬ ይህንንም ጉዳይ የሚያጣራ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አንድ ግብረ ኃይል መቋቋሙንና በዛሬው ዕለትም ወደ ኢሚግሬሽንና ወደ የለይቶ ማቆያ ሆቴሎችና ተቋማት በመሄድ እንዲያጣራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በለይቶ ማቆያዎች ጥብቅ ቁጥጥር መኖሩን የገለፁት ዶ/ር ፈይሳ፤ የፌደራል ፖሊስ ተመድቦ በየቀኑ ቁጥጥር እንደሚደረግና ግለሰቦቹ ከሚገኙበት ክፍል እንደማይወጡ ገልጸዋል።

የህክምና ክትትሉም ሆነ የሚቀርብላቸው ምግብና መጠጥ የጤና ደንቡን በተከተለ መልኩ መሆኑንም አስረድተዋል።

ዶ/ር ፈይሳ ሁሉም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ሰዎች በተለየ ክፍል ውስጥ እንዳሉ ገልፀው፤ በአንድ ክፍል ከአንድ በላይ ሰዎች ይገኛሉ የተባለው ሀሰት መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከግዴታ ለይቶ ማቆያ በሚወጡ ሰዎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ተዘግቧል።

LEAVE A REPLY