ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው ወንድማችን ቴዎድሮስ ኃይሌ ዳኘ በድንገት ህይወቱ አልፏል። ቴዲ በአትላንታ ለረጅም ጊዜ የምትታተመውንና በኖርዝ አሜሪካ ቀዳሚ የሕትመት ውጤቶች አንዷ የሆነችውን ድንቅ መጽሔት ከ15 ዓመት በላይ አዘጋጅቷል። ቴዲ በአለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት ያተረፈው አድማስ ሬዲዮ ፕሮዲዩሰር እና ዋና አዘጋጅ በመሆን ለአስር ዓመት ማህበረሰቡን አገልግሏል።
ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ኃይሌ ዳኘ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ወገኖች ጋር በመሆን በተለይ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የተመሰረተው የሰብአዊ መብት ድርጅት ጋር በለጋ እድሜው ተቀላቅሎ በሀራችን የሰብአዊ መብት እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በኢትዮጵያ የሚታተሙ የነፃ ፕሬስ ውጤቶች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ለፕሬስ ነጻነት ተሟግቷል። ጮሗል ተንገላቷል።
በስደት በአሜሪካን ሀገር አትላንታ ከተማ እግሩ ከረገጠበት ጊዜ ጀምሮ ህይወቱን እስካጣበት የመጨረሻዋ እለት ድረስ ማህበረሰቡን ያ…ለ…መ…ታ…ከ…ት አገልግሏል። አዳዲስ መጪዎችን ተቀብሏል፣ አስተናግዷ፤ የተቸገሩትንም ረድቷል፣ አስጠግቷል፤ ሀገር አውቀው በእግራቸው አስኪቆሙ አለኝታነቱን አሳይቷል። መረጃ ላጡ ሰዎችም ያለመሰልቸት ቀን ሳይምርጥ ሌሊት ደፋ ቀና ብሏል፤ የሚጠበቅበትንም ያለመታከት አካፍሏል፣ አጋርቷል።
ዘመድ ወዳጅ ሳይል፤ የቅርብ የሩቅ ሳይመርጥ፤ ዘር ቀለም፣ወይንም እስላም ክርስቲያን፣ ሳይለይ እንግዶችን በወግ በማዕረግ አስተናግዷል ።
የቴዲ የስንብት ሰነ ሥርዓት ዛሬ አርብ April 3 ቀን 220 ዓ/ም አሁን ባለው አስከፊ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት ሁሉ ነገር ተገድቦ በአትላንታ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በተዘጋጀው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ (የፓርኪንግ ሎት) ውስጥ ባለቤቱ ራሔል እና ወዳጅ ዘመዶች በተገኙበት የወቅቱን የመራራቅ ሕግ በተከተለ መልኩ ተፈጽሟል።
የቀብር ስነስርአቱ በመጪው እሁድ በጣም ውስን በሆኑ ካህናትና ቤተዘመዶች ብቻ አስር ሰዎች በተገኙበት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጸሎተ ፍትሃት ተደርጎ የቀብር ስነስርአቱ ይፈፀማል።
ቴዲ ብቻውን ሆኖ ብዙዎችን ሰብስቦ ቀብሯል
ቴዲ አንድ ሆኖ በርካቶችን አስከትሎ የአደዋን ተራራ ምሳሌ በአትላንታ ፈጥሯል
ቴዎድሮስ ዳኘ እልፍ አሰልፎ ታልቁን ሩጫን በአትላንታ እብቅሏል።
ዛሬ ቴዲ ብዙ ሰው ቢኖረውም በዘመን አመጣሹ በሽታ ምክንያት በትንሹ ሆነው ሸኝተውታል
ቴዎድሮስ ኃይሌ ዳኘ በርካቶችን ነፃ ለማውጣት በብዙ ሲደክም ቆይቶ ብዙ ሰው ቢያፈራም ጥቂቶች ብቻ ይቀብሩታል።
ለባለቤቱ ራሔል እና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ለጨቅላ ልጆቹ ለኪያ እና አልአዛር አምላክ ከለላውን ያድርግላቸው።
ባርኔጣዬን አውልቄ እጅ ነስቻለሁ ወንድምዓለም
እግዚእብሔር አምላክ በቀኙ ያድርግህ!!