ከ”እኔ ለጣና” የካናዳ እምቦጭ ግብረ ሃይል የተሰጠ መግለጫ

ከ”እኔ ለጣና” የካናዳ እምቦጭ ግብረ ሃይል የተሰጠ መግለጫ

ክፉ ዘመን እራሱን ደግሟል፤

የሰሞኑ ጉንፋን መሳይ በሽታ COVID-19 ዓለምን ብርክ ውስጥ ከቷል። ብዙ ሽህ ሕዝብ በበሽታው ተጠቅቷል። ለብዙ ሕዝብ ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። የዓለምን ኢኮኖሚ አድቅቋል። በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከስራ አሰናብቷል፤ ማህበራዊ ኑሯችንን አቃውሷል። አይነኬውን እና ሃያሉን ሃገር ሁሉ ብርክ ውስጥ ከቷል።

ዓለም ይህን መሳይ ወረርሽኝ ስታስተናግድ የመጀመሪዋ አይደለም። በ1918 ተመሳሳይ ወረርሽኝ በስፔን ተከስቶ የ50 ሚልዮን ሕዝብ ሕይወት ቀስፏል፤ 500 ሚልዮን ሕዝብ በበሽታው ተጠቅቷል (https://www.cdc.gov/flu/pandemic-resources/1918-pandemic- h1n1.html)። ልጅ ሆነን ወላጆቻችንና አያቶቻችን ቀባሪ አታሳጣኝ እያሉ ሲመርቁ፤ የወረርሽኙ ዘመን እያሉ ሲአወሩ ተረት መስሎ ይታየን ነበር።

በእኛ እድሜና ዘመን በተረት የሰማነው ክፉ ጊዜ ይከሰታል ብለን አስበን አናውቅም ነበር። በፈንጠዝያ፤ በአስረሽ ምችው፤ በቴክኖሎጂ፤ በሃብት፤ በስልጣን እና በጉልበት ታብየን የፈጣሪን ቁጣ ዘነጋን። በፈጣሪ ቁጣም ስንገታ ቁጭ ብለን አየን።

ቁጣውም ባለስልጣን ከጭቁን፤ ድሃ ከሃብታም፤ ብርቱ ከደካማ፤ አገር ከአሃጉር ሳይለይና ድንበር ሳይገድበው ዓለምን በሙሉ ቀሰፈ። ጥፋቱ የሁላችን፤ መቅሰፍቱ የጋራችን ሆኗል። ለዚህም ነው COVID-19 ቀድስት ሃገር ኢትይጵያን ያጠቃው። አፍንጫን ሲነኩት ዓይን ያለቅሳል እንዲሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሃገራቸውን መጠቃት እንደሰሙ እንዴት መርዳት እንዳለባቸው በየአካባቢው፤ በየቤተ እምነቱ፤ በየመኖሪያውና በየአጋጣሚው ሲወያዩ ቆይቷል።

በኢትዮጵያ የወረርሽኙን መጠን በውል ባናውቅም ከመንግስት መረጃ እንደሰማነው ለጊዜው መለስተኛ እንደሆነ ነው። ሆኖም ሁኔታው ባጭር ጊዜ የተለየ መልክ ሊይዝ እንደሚችል በማሰብ ወገኖቻችንን ከዚህ ወረርሽኝ መታደግ እንደሚገባ ግንዛቤ ወስደናል።

ስለሆነም ”እኔ ለጣና” ከተሰኘው ከሞንትሪዮል፤ ካልጋሪ፤ ሃሊፋክስ፤ ቶሮንቶና ኦታዋ የተውጣጡ የእምቦጭ ግብረ ሃይል አባላት መጋቢት 20, 2012 አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በጉዳዩ ላይ በጋራ መክሯል። ከካናዳ ጓንት፤ የፁዳት እቃዎች፤ የአፍ ጭምብል ገዝቶ መላክ እንደሚአስፈልግ ብናምንም በካናዳ የቁሳቁሶች አቅርቦት እጥረት መኖሩን ተገንዝበናል። መግዛት ቢቻል እንኳን የየብስ እና የአየር መጎጓዣ ዝግ በሆነበት ሁኔታ ለወገን ማድረስ አይቻልም። ከኢምባሲ ለማወቅ እንደቻልነው የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና መድሐኒት ፋብሪካዎች እነዚህን ቁሳቁሶች ስለሚአመርቱ በገንዘብ መርዳት ተመራጭ ሆኖ ተገኝቷል። ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የገንዝብ ድጋፍ እንዲአደርጉ አስበን ነበር።

በወረርሽኙ ምክንያት የኢትዮ-ካናዳዊያን እንቅስቃሴው የተገታ በመሆኑ ሕዝቡን በአስቸኳይ ማሰባሰብ ባለመቻሉ ይህን አስቸኳይ እርዳታ ለግሰናል። በቅርቡ የቴሌኮንፈራንስና እስካይፕ ጥሪ አድርገን ተጨማሪ እርዳታ የምናሰባስብ ሲሆን ለድጋፋችሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንጊዜም የሚመካባችሁ መሆኑን እንድታውቁት ይሁን።

ስለሆነም የ”እኔ ለጣን” ግብረ ሃይል በካናዳ የእምቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽን ገዝቶ ለኢትዮጵያ ካስረከበው የተረፈ Ca$49,000 ዶላር ያለ በመሆኑ፤ ሕይወት ማትረፍ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ስላመንበት ካለው ገንዘብ ላይ Ca$45,000 ዶላር ወጪ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲታገዝ ተወስኗል።
ገንዘቡ የሚላክበትን መንገድ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ተነጋግረን መስመር እንዳስያዝን በሂደት ለደጋፊዎቻችን የምናሳውቅ መሆኑን እንገልፃለን። ክፉ ዘመን ራሱን ቢደግምም በህብረትና በአንድነት ቆመን፤ በግዚአብሔር እምነት ፀንተን ይህን ክፉ ጊዜ እንሻገራለን።

ለተጨማሪ ማብራሪያ አቶ ሰማነህ ጀመረን

በስልክ ቁጥር 613-796-6196

ኢሜል stjtamrat@hotmail.com ያናግሩ።

ቸሩ ፈጣሪያችን ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን በምህረት ዓይኑ ይጎብኝልን ።
የ”እኔ ለጣን” ግብረ ሃይል፤ ኦታዋ ካናዳ፤ (መጋቢት 24 ቀን 2012)

LEAVE A REPLY