የሀበሾች ሞትና ኮረና! ዋሽንግተን || ደረጀ ደስታ

የሀበሾች ሞትና ኮረና! ዋሽንግተን || ደረጀ ደስታ

ኮረና ዜና መሆኑ ቀረ። ቀጥሎ ሰው ሆነ። ከዚያ ሀበሻ ሆነ። አልፎ ቀርቦም እምናውቀው ሰው እየሆነ እየሆነ….

ስሜት መግለጽ ያቅታል። ከሐዘን ልብ ቃል አይወጣም። ስሜት ግን አምጦ አስምጦ አንድ ነገር ያስብላል። ይገለጽ ነገር ያለ ይመስል ባይባል ይሻል ነበር።

ያደለው ግን ይገልጸዋል። ሐዘን እንደ ጥሩ ዜማ ይንቆረቆርለታል። እንባውም እንደጅረት ይፈሳል። ያን እምታወቀው ሰው እልፈቱን በቃል ስትገልጸው ፈገግታና አብሮ ሳቃችሁን በሳቅ እምባ አንብተህ ስታጅበው… ከቻልክበት ታድለሃል። በቁም የተቀያየምከው ሲሞት ያሳፍረሃል። በምጥን ፈገግታ በስስት የአንገት ሰላምታ ሀይ! ስትለው የኖርከውን ግን…

ያን ልጅ አወቅከው ያ…ደስ እሚል ልጅ….ዋሽንግተን፣ ቨርጂኒያ ስካይ ላይን አካባቢ ሜሪላንድ ሲልቨር ስፕሪንግ እምታውቀው ልጅ … ያ ምነው አንድ ጊዜ እንኳ ….አዎ አዎ….
ሞተ እኮ!

ተቀሽቀዳድመህ ፎቶውን ሶሻል ሚዲያ ላይ ትፈልገዋለህ። መቶ በመቶ አረጋገጥክ እሱ ራሱ ነው። እንደገና ይሞትብሃል!!!!

እንግዲህ የት ሄደህ ታለቅሳለህ? በለቅሶ ባህላችን፣ በትልቁም በትንሹም ለምናውቀው ማልቀሳችን አንድም ለካ የጸጸት ነው።

ምነው ይቅር ባልኩት፣ አግኝቼ ጭምቅ አድርጌ ባቀፍኩት፣ ሞቅ አድርጌ ሰላም ባልኩት፣ ባልተጀነንኩበት። እንዲህ እሚያስለቅሰኝ ከሆነ….
የሀበሻ ሰላምታ ሁለት ነው። አንዱ ሞቅ ጭምቅ ጠብ እርግፍ እቅፍቅፍ የሚያስደርግ ሲሆን፣ ሌላኛው “ሶሻል ዲስታንሲንግ” ነው… ኩርት ልጥጥ ብሎ ሰላም በመባባልና ባለመባባል መካከል ያለ። ወይም እንደፈረንጆቹ ፈገግታ ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል።
እንዲህ ብልጭ አድርጎ ድርግም ለሚያደርገን፣ እንዲህ ብርክ አስይዞ ለሚያስጨንቀን ኃላፊ ሕይወት፣ የፖለቲካው እንቶ ፈንቶ ይቅር… በማህበራዊ ህይወታችን እንኳ መራራቃችን፣ በትንሽ ቡድን እየታጠርን መቅረታችን ለምን ይሆን? …. ይህ ሁሉ ከአንገት በላይ ሰላምታ መገለማመጥ፣ መካሰስ፣ መነካከስ ተጠፋፍተን ለማንጠፋፋው፣ ጉንፋን ቫይረስ ለሚያጠፋን…. ምን ሆነናል?!
እማውቅህ እምታውቀኝ ሀበሻ ወዮልህ ከእንግዲህ አለቅህም። አቅፌ ብጠግብህ፣ ጨምቄ ባልጨርስህ ምን አለ በለኝ። ይህ ቀን ይለፍ። የሰው ነፍስ ይዞ ማለፍ ካለበት ግን ያንተን ቀን ለኔ ያድርገው። ወገኔ ውለህ ግባ!

“እኔስ ውሸቴን ነው አልወዳትም ያልኩት” አለ ዘፋኙ። ውሸት ነው ሀበሾች እንዋደዳለን። እንዲህ ለመተዛዘን ግን በሞት እቅፍ መሆን የለብንም። ኮረና ይጨረሰን ዘንድ ግድ ከሆነ ሞታችን ይጥቀመን። እንማማርበት። የልጆች የወንድም እህቶቻችንን ሞት በባዶ አናስቀረው!! እግዚአብሄርንም በምልክቱ ተምረናልና ይቅር በለን እንበለው።

LEAVE A REPLY