እጅግ የነቃችው አፍሪካዊት ሃገር “ጋና” || ሙሼ ሰሙ

እጅግ የነቃችው አፍሪካዊት ሃገር “ጋና” || ሙሼ ሰሙ

እጅግ የነቃችው አፍሪካዊት ሃገር “ጋና” የውሃ ክፍያን ለሶስት ወር ነጻ ማድረጓ፣ በሽታውን በግንባር ቀደምትነት ተጋፋጭ ለሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችና ለበሽታው ሰለባዎች እንክብካቤ ለሚያደርጉ ባለሙያዎች ማበረታቻ እንዲሆን የደሞዝ እድገት መስጠቷና ከታክስ ነጻ ማድረጓ፣ ሩቅ አሳቢ አመራር ያላት መሆኑን አመላካች ሆኖ አግኝቼዋለሁ።ወደ ጓዳችን ስንመጣ ግን አዋጡ፣ ቸር ሁኑና ተባበሩ ከማለት ባለፈ መሰረታዊና የድሃውን ማህበረሰብ ኑሮ የሚደጉሙ ተግባሮችን ከመፈጸም አኳያ፣ ኋላ መቅረታችን ወይም አለመጀመራችን የቅድመ ዝግጅት ማነስና ችግሩን አጥብቆ ያለመፈተሽ አባዜ እንዳይሆን ሰግቺያለሁ።

ኢኮሚያዊ ዳሰሳ ላይ ተመስርቶ ድጎማ ማድረጊያው ጊዜ፣ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። ከአቅም አኳያ ሙሉ ለሙሉ ከክፍያ ነጻ ማድረግ ባይቻል እንኳን ለሚቀጥሉት ወራት የውሃና የመብራት ክፍያዎች በረጅም አከፋፈል ስርዓት በማደላደል፣ ደመወዝን በተዘዋዋሪ መንገድ መደጎም ይገባል። ለደሞዝተኛው በተለይ የታክስ ሽግሽግ ማድረግም አስፈላጊ ነው። ለጤና ባለሙያዎችና ከበሽታው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎች፣ በበሽታው ቢያዙ ጥገኞቻቸውን ለመርዳት የሚያስችላቸው ቃል ኪዳን” መንግስት መፈረም አለበት። በጥናት ላይ ተመስርቶ ሌሎች መንግስታዊ ግዴታዎችን ወይም ክፍያዎችን ጊዜ ማራዘም ይቻላል። “እንካ-ን የማያውቅ፣ አምጣን ማን አስተማረው እንዲሉ፣” ካለው ማካፈልን ያልጀመረ መንግስት አዋጡና ስጡን ለሕዝብ ሊያስተምር አይችልም።

ሃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ብዙም ርቀን ሳንሄድ መዝረክረክና መዛል ጀምረናል። የምንችለውን እያደረግን ነው ማለት ብቻ መፍትሔ አይሆንም። ከውጥረትም ሆነ ከአቅም ማነስ የሚፈጠር ክፍተትን ለመሙላት አቅም ያለውን መጋበዝ፣ ማካተትና ማማከር ያስፈልጋል።

እንደተለመደው የሕግ አስፈጻሚዎቻችን ያዝ ለቀቅና ሙስና ዛሬም በማገርሸቱ ስግብግብ ነጋዴዎች መጫወቻ እያደረጉን ነው። ምርት ማምረት የቆመ ይመስል የእህል ዘር ገበያ ላይ የለም፣ አለ ከተባለም ዋጋው የማይቀመስ ነው።

እንደ ጥቆማ፣ ኮቪድ 19 ከዕለት የዕለት ስራ በላይ ማሰብ ማስተዋል መቆርቆር የሚጠይቅ ውስብሰወብ ችግር ነው። የተቀናጀ፣ አርቆ የሚመረምር፣ መሰረታዊ ችግሩን የፈተሸና መፈትሔ ማፍለቅ የሚችል ሃገራዊ ኮሚቴ ይቋቋም፣ እንደ “አደጋና ዝግጁነት ኮሚሽን” ያሉ የካበተ ልምድ ያላቸው ተቋማት ከተኙበት ይቀስቀሱ፣ ዘመናዊ አሰራርም ይዘርጋ። ዘለቄታ ያለው ስትራቴጂ በአጭር ጊዜ፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ከፋፍሎ ማዘጋጀትም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው። ካልተጀመረ ይጀመር ።

LEAVE A REPLY