ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶችንና ትምህርት ቤቶችን ከዐሥራ አምስት ቀን በፊት የዘጋው የአዲስ አበባ መሴተዳደርን ጨምሮ ፌደራል መንግሥቱ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከቤት እንዳይወጣ የሚያደርጉ ስልቶችን እየተጠቀመ ይገኛል::
እስካሁን ድረስ የኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ የተመዘገበበት የአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚታየው መዘናጋት በእጅጉ አሳሳቢ የሆነበትና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በቅድመ መከላከል የተቀመጡት መርሆዎች አለመተግበራቸው ያስጨነቀው መንግሥት ኮሮና በኢትዮጵያ ወስጥ የሞት አኃዝን ማስረከቡን ተከትሎ በይፋ ከቤት አትውጡ ባይልም የሕዝብን እንቅስቃሴ የሚገቱ የተለያዮ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል::
ከእነዚህ መመሪያዎች መሀል ከነገ ጠዋት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው የአዲስ አበባ ታክሲዎች ስድስት ሠው ብቻ እንዲጭኑ የሚያስገድደው ህግ አንዱ ነው:: አብዛኛው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸው በቤት ሆነው ሥራቸውን እንዲሠሩ ማድረጋቸውን ተከትሎ አሁን ላይ ከቤት በመውጣት ወደሥራ የሚሄዱት የግል ድርጅት ሠራተኞች ብቻ ስለሆኑ የትራንስፖርት እጥረትን በከተማዋ በመፍጠር ሕዝቡ በራሱ ጊዜ ከቤት እንዲቀር እየተሠራ ይገኛል::
ቅዳሜ ዕለት ከንቲባ ታከለ ኡማ ነዋሪውን ከቤት እንዳይወጣ መንግሥት የመገደብ ሐሳብና ፍላጎት እንደሌለው ቢናገሩም ትናንት የደረሰው የሞት ክስተት መንግሥት በተዘዋዋሪ ሕዝብ ከባቱ እንዳይወጣ የሚያስገድደውን አማራጭ እንዲጠቀም አድርጎታል::
ተግባራዊ በሚሆነው ስድስት ሰዎችን በሚጭነው የአዲስ አበባ ታክሲዎች አሠራር ማንኛውም ግለሰብ ቀደም ሲል ለትራንስፖርት የሚያወጣውን ገንዘብ እጥፍ መክፈል ግድ ይህኖበታል::