ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሞት ዜና ከተሰማበት ቀን በኋላ የፍርኃት ድባብ የሰፈነባት አዲስ አበባ ውስጥ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ንክኪ አላቸው በሚል የተጠረጠሩ ሰዎች በፀጥታ ኃይላት አማካይነት ከመኖሪያና ከሥራ ቦታቸው እየተያዙ ናቸው:።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ መንግሥት መግለጫዎች አውጥቷል። በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ የሞት ዜናዎች ሊሰሙ እንደሚችሉ መጠቆሙ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል።
በኮሮና የሚጠረጠሩና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን በተደጋጋሚ ያሳወቀው መንግሥትም በደረሰው የሞት አደጋ መደናገጡን እና ሌሎች በፅኑ የታመሙ ሰዎችም መኖራቸው ሀገራዊ ስጋቱን ከፍ ያደረገው መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ከትናንት ማምሻ ጀምሮ አስቀድመው ወደ ማቆያ በገቡ ተጠርጣሪዎችና ሕሙማን አማካይነት ንክኪ አላቸው በሚል የተጠቆሙ ግለሰቦችን በፍጥነት የማደን እርምጃ ተወስዷል::
በዚህ ውስጣዊ መመሪያ መሠረት የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጣጠር በተዋቀረው ግብረ ኃይል አማካይነት ትናንት ከምሽቱ ሁለት ሰዐት በኋላ በመዲናዋ በርካታ ቦታዎች የመብራት ኃይል አገልግሎት ተቋርጦ የአሰሳና የመያዝ ተግባር መፈጸሙን ጥቆማዎች እየወጡ ነው።
በትናንቱ ዘመቻ የተያዙትና ወደ ለይቶ ማቆያ የተወሰዱት ግለሰቦች አብዛኞቹ ቀደም ሲል ወደ ማቆያ ከተወሰዱ ሰዎች ጋር በሦስተኛና በአራተኛ ወገን በኩል ግንኙነት ወይም ንክኪ ይኖራቸዋል በሚል ተጠርጥረው በዝርዝር ውስጥ የሰፈሩ መሆናቸውን ከደረሰን ዜና መረዳት ተችሏል::
ዘመቻው ዛሬም ቀጥሎ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ከሥራ ቦታቸውና ከመኖሪያ ቤታቸው እንደ ተወሰዱ የጠቆሙት ምንጮቻችን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ24 ሰዐት ውስጥ ምርመራ ካደረግኩባቸው 164 ሰዎች ውስጥ አንድ ሰው ብቻ ቫይረሱ ተገኝቶበታል በማለት የሰጠው መግለጫ ውስጥ የተካተቱት ሰዎች ትናንት ምሽት መብራት በማቋረጥ በተወሰደው ዘመቻ እንደሆነ ምንጮቻችን ጠቁመውናል።