በኮቪድ 19 የተጠረጠሩ 5 ሰዎች ከሰታዲየምና ግንፍሌ አካባቢ በፀጥታ ኃይሎች ተወሰዱ

በኮቪድ 19 የተጠረጠሩ 5 ሰዎች ከሰታዲየምና ግንፍሌ አካባቢ በፀጥታ ኃይሎች ተወሰዱ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ አምስት ሰዎች ከስታዲየም እና ከግንፍሌ አካባቢ በፀጥታ ኃይሎች አማካይነት መወሰዳቸው ሪፖርተራችን ከስፍራው አረጋግጧል።

አስቀድመው በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩና (አንዳንዶቹም በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ) ለምርመራ የሚፈልጉ ሰዎች በተለያየ መንገድ ቀደም ሲል ወደ ማቆያ የገቡ ሰዎች የጠቆሟቸው መሆኑን የዜና ምንጮቻችን ገልጸዋል::

ከተለያዮ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ሰዎች ጋር ንክኪ አላቸው በሚል ከተጠረጠሩት ሰዎች መሀል ቀደም ሲል በተሰጠው አድራሻቸው ሊገኙ ያልቻሉ ሁለት ጥንዶች በፀጥታ ኃይሎች ክትትል ስታዲየም አካባቢ ባለ አንድ የትርጉም ሥራ የሚሠራ ቢሮ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ግለሰቦቹ ላለፉት ዐሥር ቀናት ሲፈለጉ እንደነበር ያጣራው ሪፖርተራችን ቀደም ሲል የተመዘገበው አድራሻቸው (የሥራ ቦታ) የተዘጋ መሆኑና መኖሪያቸው በውል አለመታወቁ ጥቆማውን አደብዝዞት የነበረ ቢሆንም ከሌላ ወገን በተገኘ መረጃ ግለሰቦቹን በትርጉም ሥራ ቢሮው ውስጥ ለመያዝና ወደ ለይቶ ማቆያው ለመውሰድ ተችሏል።

ተጠርጣሪ ጥንዶቹ በተያዙበት ወቅት ቀጥታ አካላዊ ንክኪ አድርጋለች በሚል አንዲት የትርጉም ቤቱ ጸሐፊና ለተመሳሳይ ሥራ በስፍራው የተገኘ አንድ ወጣትም ለምርመራ ወደ ለይቶ ማቆያው መወሰዳቸውን የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ለጉዳዮ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦችን አነጋግሮ ማረጋገጥ ችሏል።

በተመሳሳይ ዜና በተለምዶ ግንፍሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነ የ34 ዓመት ወጣት በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥሮ ከመኖሪያ ቤቱ በፀጥታ ኃይሎችና በሕክምና ቡድን አባላት መወሰዱን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቀዋል።

ወጣቱ አስቀድሞ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩና እና በለይቶ ማቆያ ከተቀመጡ ሰዎች ጋር ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ንክኪ ይኖረዋል በሚል የተደረገውን ጥቆማ መሠረት በማድረግ ነው ዛሬ ጠዋት ከመኖሪያ ቤቱ የተወሰደው። በዚህ አካባቢ ከ17 ቀን በፊት ከዱባይ የመጣ አንድ ወጣት የኮሮና ቫይረስ ምልክት ይታይብኛል በሚል ያደረገውን ጥቆማ ተከትሎ ወደ ለይቶ ማቆያ የሕክምና ስፍራ መወሰዱን ታማኝ የዜና ምንጮቻችን ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY