መለስ ዜናዊን በመሞገት የሚታወቁት አቶ ተመስገን ዘውዴ አረፉ

መለስ ዜናዊን በመሞገት የሚታወቁት አቶ ተመስገን ዘውዴ አረፉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የቅንጅት ለአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራርና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ተመስገን ዘውዴ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰማ።

በታሪካዊው ምርጫ 97 ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው የቅንጅት አባል የነበሩትና በወቅቱ በተካሄደው ምርጫ አሸናፈው ለአምስት ዓመታት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ተመስገን ዘውዴ ለረዥም ጊዜያት ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት የአልጋ ቁራኛ ሆነው ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ነበር።

በአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮችና በተለይም  የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በተደጋጋሚ ያለ ፍርኃት በመሞገትና በመከራከር የሚታወቁት አቶ ተመስገን ዘውዴ በምክር ቤቱ ውስጥ በሚያሰሟቸው በሳል አስተያየቶች በብዙኃኑ ኅብረተሰብ ዘንድ ተወዳጅነትን ማግኘታቸው አይዘነጋም።

በደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት በሳውላ ዞን “ቡልቄ ” ተብላ በምትጠራ አካባቢ ነው የተወለዱት አቶ ተመስገን ዘውዴ።  በአሜሪካ ዳላስ ከተማ በሚገኝ የንግድ ኮሌጅ ውስጥ በንግድ ሥራ አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙ ሲሆን 22 ዓመታት በኖሩባት አሜሪካ ትዳር መስርተው አንድ ልጅ ወልደው እንደነበር የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።

ህወሓት መራሹ መንግሥት አዲስ አበባን መቆጣጠሩን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ገብተው እንዲሠሩ ያቀረቡትን ጥሪ አምነውና ተቀብለው አሜሪካዊት ባለቤታቸውንና ልጃቸውን እዛው ትተው “ቅድሚያ ለሀገሬ” ሲሉ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት።

ይሁን እንጂ ሀገር ቤት ከደረሱ በኋላ እንዳሰቡት  ለመሥራት የሚያስችል ነፃነትና የፖለቲካ ምኅዳር ባለማግኘታቸው፣ ሥርዓቱም ዘረኛና አምባገነን መሆኑን በመረዳታቸው ቅንጅትን በመቀላቀል በሠላማዊ መንገድ ፖለቲካዊ ትግል አድርገው የፓርላማ አባል መሆን ችለዋል።

ዛሬ ሕልፈተ ዜናቸው የተሰማው አቶ ተመስገን ዘውዴ ከሁለተኛዋ ኢትዮጵያዊት ባለቤታቸው ሁለት ልጆችን ለማፍራት በቅተዋል።  በታላቁ ፖለቲካኛ አቶ ተመስገን ዘውዴ ሞት ኢትዮጵያ ነገ ዝግጅት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸውና   ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ልባዊ መፅናናትን እንመኛለን።

LEAVE A REPLY