ቴ(ዎ)ድሮስ አድሓኖምና WHO || መቅደስ መስፍን

ቴ(ዎ)ድሮስ አድሓኖምና WHO || መቅደስ መስፍን

ሰውዬው ወያኔ ሆኖ ሲኖር ለብዙ ዓመታት በተለያየ ግዜ የተለያዩ አሰቃቂ ነገሮች ሲፈጸሙ (ወይም ባግባቡ ሳይፈጸሙ በመቅረታቸው ሕዝብ ሲንገላታና ሲበደል ) አይተናል። ለሕዝብ ደህንነትና ሙሉ ጤና እተጋለሁ የሚል ሰው እንደዚህ ዓይነት ተሳትፎ ኖሮት ሲገኝ ሕዝብ ዘንድ ቁጣም ቁጭትም የእምነት መጉደልም ሊቀር እንደማይችል ማወቅ አለበት። ሰውዬው ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ጸሐፊነት ራሱን ሲያጭ ከገዛ ወገኑ ያ ሁሉ ተቃውሞ ቀርቦበት የነበረውም በዚያም ቁጭት ምክንያት ነው። እንዴት ያንን እንዴት ተቋቋመና ለዚያ ኃላፊነት ተሰየመ?

እኔ እንደሚገባኝ ሦስት ነገሮች ረድተውታል። አንደኛው የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ እኛ በአገራችን ለብዙ ዓመታት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስፋት መፈጸማችውን ለማሰማት በተለያየ ግዜ ስንማጸን በነበረ ግዜ በተደጋጋሚ እንዳስተዋልነው የራሱ ጉዳይ ከበለጠበት የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ቀለል ያለ ክብደት ሰጥቶ የኢትዮጵያን መንግሥት ለሚፈልጋቸው ነገሮች አገልጋይ አድርጎ እያኖረ ያዳበረው ዝምድና ነው። ሁለተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ አፍሪካዊ ቦታው ላይ በማስቀመጥ ሰዎችን በእኩልነት እንደሚያወዳድር ማሳያ (ቶክን) መፈለጉ ነው። ሦስተኛው ሰውየው በሙያው ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጽሟል የሚባልለት ብቃት ያሏችው የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሥራ ፍጻሜዎች ናችው። እኔ በቦታው አልነበርኩም። ያዩና የነበሩ ብዙ ይሉለታል። (ያንንና ሌሎችም ሥልጣኖችን በመጠቀም ፖሊቲካዊ ጥፋት ጠፍቷል አልጠፋም የዚህ ሦስተኛ ነጥብ ጉዳይ አይደለም። ይህ ነጥብ የተመለከተው እውቀትና ሙያ አለው ወይ የለውም የሚለውን ጥያቄ ነው)

የኢትዮጵያ መንግሥት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆኖ ሙያውን የተወጣውን ያሀል፣ የኢትዮጵያ አገዛዝ የነበረው የወያኔ ድርጅት ከፍተኛ አካል ሆኖ ኖሯል። በዚህ ሰዓት የተፈጸሙ ልክ የሌላቸው በደሎች እስከዛሬ ፍትሕ አላገኙም። በወቅቱም ወያኔ መሆኑ እንደሚያኮራው ሁሉ የገለጸባቸው ግዜዎች ጭምር አሉ። በተጨማሪ የወያኔ መንግሥትና ባለሥልጣናቱ ከቻይናና ከሌሎች መንግሥታት ጋር በኤንቬስትመንት ሰም የፈጠሩት ዝምድናም አገሪቱን በዝብዞ፣ ሕዝብን በድሎ እነሱን በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል።
በሌላ በኩል ቻይና ባላት የኢኮኖሚ ኃይል ተጠቅማ የራሷንና የወዳጆቿን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሬከርድ ዋጋ እንዳይሰጠውና የፖሊቲካና ሌሎች ውሳኔዎች ላይ ግምት እንዳይገባ ተፅዕኖ የሚያደርግ መንግሥት ያላት አገር ናት ።

በዚህም ዓመሏ በሽታው ተሰራጭቶ ዓለምን ካዳረሰ በኋላ ድሮ የደረሰችለት የፖሊቲካ አጋሯ የወያኔ ድርጅት አባሉ ቴዎድሮስ አድሓኖም ባደባባይ በኮሮና ቫይረስ ላይ ቻይና ለወሰደችው “ፈጣን እርምጃ” አወደሳት።

ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ትራምፕ አለ።

ትራምፕ ባለፈው ሕዳርና ታህሳስ አካባቢ ቻይና የተከሰተን አንድ አዲስ በሽታ እየደበቀች መሆኑንና ይሄም አደጋ እንዳለው ያገሪቱ የስለላ ድርጅት ባለሙያዎች ነገሩት ። ነገሩን ሰውየው ከቁም ነገር አላስገባውም።

ከዚያም በሽታው አሜሪካ ገባና ዛሬ በዓለም ካሉት 1 ነጥብ 7 ሚልዮን በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች መሃል ባሁን ሰዓት ግማሽ ሚልዮኑ ማለትም ከሩብ በላይ አሜሪካ ይገኛሉ። (የቻይና ቁጥር አሁንም አከራካሪ ነው) አሁን ትራምፕ የሱ ችልተኝነትና የኢኮኖሚው መዳሸቅ ያደረሰበት የፖሊቲካ ክስረት አስጨንቀው ይዘውታል። ስለዚህ የሚያሳብብበት ሲፈልግ ቻይናንና የአድሓኖምን ልጅ አገኘ። (እሱ ከስለላ ድርጅቶቹ የተሰጠው መረጃ አንዳልነበረ ሆኖ ማለት ነው።)

ዋና ፀሐፊውና ደጋፊዎቹ ይህን ግዜ እሱ ላይ ጣቱን የቀሰረን ሰው ሁሉ በዘረኝነት ይወነጅሉ ጀመር። በተወሰነ ደረጃ ትክክል ናቸው። የትራምፕ ደጋፊዎች አንድ አፍሪካዊ ለነሱ ፖሊቲካ ፍጆታ ቢሰዉ ግድ አይሰጣቸውም። እንዲያውም ይህን ሊመርጡ ይችላሉ። ቻይናን ግን ለኢኮኖሚያቸው ይፈልጓታል።

ከዚያ በተረፈ በዚህ ሥራ ባስፈታን ግዜ ጎራ ለይቶ አሱ ላይ ያቀሳሰረውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በዘረኝነት ለመወንጀል ጥርሱን የነቀለበት ድርጅት አባል ሆኖ እንዴት ይችላል? አይችልም! ደጋፊዎቹም አይችሉም!

ደጋፊዎቹ ስል ደግሞ ሌላ ኃይል ማንሳት አለብኝ። ለብዙ ዓመታት ሲያማርሩት፣ ሲወቅሱትና ሲቃወሙት፤ የነበረበትን የዘረኛ መንግሥት ሲኮንኑ ኖረው ዛሬ በሙያውና ባለበት የኃላፊነት ቦታ ላይ በመድረሱ የሚያመሰግኑት ሰዎች እንዴት ተቃጣበት ብለው የሚያሰሙትን ስሞታ የዘረኝነት ውጤት ነው ብለው እንደሚያምኑ ይገልጹልናል። እነሱም እንደሌላው ወገን የተቃውሞውን መንስዔ ሲፈትሹ የሰውየውን ጥቁርነት ከማንሳት በተጭማሪ በምን ተግባር ተወቀሰ ብለው በአግባቡ መመርመር እንዳለባቸውና ዘረኝነት ለሁሉ ጥያቄ መልስ እንደማይሆን አላወቁም። ይሄንንም አንዘንጋ።

እሱ ላይ የተነሳበት ኢትዮጵያዊ ኃይልም መመርመር ያለበት ነገር አለ። ይህን ኃላፊነት መወጣት አይችልም የሚሉት ብቃት የለውም ነው? ወይስ ወያኔ ነው ነው? የብቃቱ ጉዳይ ማስረጃዎች የቀረቡበት ስለሆነ የሶሻል ሚድያው ሙግት ዋጋ የለውም። ወያኔ ነው ከሆነ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ከሆነም በውሳኔው ሰዓት እንጂ አሁን ወያኔነቱ ጉዳዩ አይደለም። ጥያቄው እሱ አይደለም።

ባሁን ሰዓት የወያኔን ዘረኝነት ኮንኖ የትራምፕን መደገፍ፤ የወያኔን በቀለኝነት ኮንኖ የተቃዋሚዎቹን በቀለኝነትን ማለምለም (እዚህ ጋ ምክንያታዊ ያልሆነ ተፀዕኖ በቀል ብቻ ነው። ፍትሕ ሌላ መድረክ ይፈልጋል) የሚያስኬድ አይሆንም።

ግዜ የተፈታተነው ላይ ተረባርቦ ከማቀሳሰር የሚሻለው “የአሠራር ብልሹነት አለ ወይ?” “ካለስ ምን ይመስላል?” “የበሽታው በስፋት መሰራጨትስ ላይ ምን ተፅዕኖ አሳርፏል?” የሚለውን ብንፈትሽ ነው። ሰውዬውን ሳይሆን ግብሩን መመልከት ብንጀምርስ? የምንወደው ወይም የማንወድደው ብለን ስንነሳ የምንሰጠው ግምት የስሜት ጭነት እንዳይኖረው ብንጠነቀቅስ?

ሰውዬው ኮሌራ በሽታ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ለመደበቅ ሲጋጋጥ እንደነበር ዓለም ያውቃል። እኛም በስንቱ የበደል ሰዓት ሰንጮህ እንደነበር ዓለም ያውቃል። ግን ቦታውን እንዲይዝ “ዓለም” ፈቀደለት ። አሁን ቻይና የኮሮና ቫይረስን ሁኔታ ደብቃ ማቆየቷ እንዳለ ሆኖ “ለፈጣን እርምጃዋ” በገሃድ አሞገሳት ። አመል አይለቅ! ዛሬ ደግሞ የሚሰማው ይብሳል። ከቻይና በሽታው ተስፋፍቶ ወደሌሎች አገሮች መዛመት ሲጀምር አንዳንድ አገሮች የወሰዱትን እርምጃ ተቃውሞም ነበር! ሥራው ያውጣው እንግዲህ! (ዘሩ ወይም ፓርቲው ወይም የኢትዮጵያ ፖሊቲካ አላልኩም)

LEAVE A REPLY