ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚል አዲሱ አትክልት ተራ የሆነው ጃን ሜዳ ገና በቀናት እድሜ ውስጥ በቆሻሻ መበከሉና ለኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ አስጊ መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከወዲሁ በመግለፅ ላይ ናቸው።
ለበርካታ ዓመታት ጊዮርጊስ ከአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ዝቅ ብሎ የሚገኘው ግዙፉ የአትክልት መሸጫ ቦታ ከመጠን በላይ የተጨናነቀ መሆኑን ተከትሎ በከንቲባ ታከለ ኡማ ልዮና አስቸኳይ ትዕዛዝ ወደ ሠፊው ጃን ሜዳ ተዘዋውሮ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ አትክልት ተራው ወደ ጃን ሜዳ ቢዛወርም መመረያውና አሠራሩ ያልተጠናና ቅድመ ጥናትን የተመረኮዘ ባለመሆኑ ከጅምሩ ወደ አስከፊ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን መታዘብ ችለናል::
በጃን ሜዳ አትክልት መሸጫውን ተዘዋውሮ የተመለከተው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ገና በአምስት ቀናት እድሜ ውስጥ አካባቢው በከፍተኛ ቆሻሻ መበከሉንና አየሩም አፍንጫን በሚሰነፍጥ ሽታ መቀየሩን መታዘብ ችሏል:: ከንቲባው የቀድሞው ገበያ የተጨናነቀ መሆኑን ተከትሎ ወደ ጃን ሜዳ እንዲዛወር ማድረጋቸው የሚበረታታ ቢሆንም ለአትክልት ነጋዴዎቹ የተሰጠው የመሸጫና የመገበያያ ቦታ በእጅጉ የተጠጋጋ በመሆኑ የታሰበውን ችግር ሊቀርፍ እንደማያስችል ነዋሪዎች በመናገር ላይ ናቸው::
“አትክልት ተራ ወደ ጃን ሜዳ ተዛውሯል መባሉ አስደስቶኝ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ወደ ስፍራው ስመጣ ያየሁት ነገር በእጅጉ አስደንግጦኛል:: ግቢው ሠፊ ቢሆንም የመገበያያ ቦታው በጣም የተጠጋጋና ከበፊቱ ፈጽሞ ለውጥ የለውም:: አሁንም ከሕዝብ ጋር እየተጋፋህ ነው የምትገበያየው ፤ ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሣሣቢ ነው” ያሉት የ58 ዐመቷ ወ/ሮ አለምነሽ መኮንን መንግሥት አትክልት ተራን ወደ ጃንሜዳ ቢያዘዋውርም በዚህም ቦታ ያለው አሠራር በኮሮና ቫይረስ ላለመያዝ የሚሰጠው አንዳችም ዋስትና እንደሌለው አስረድተዋል::
በተለይም በአምስት ቀናት ውስጥ የተከማቸው ቆሻሻ ተበላሽተው የተጣሉ አትክልትና ፍራፍሬዎች ወቅቱ ንጽህና የሚያስፈልግበትና የሚሰበክበት ቢሆም ከሚታየው የተዝረከረከ እንቅስቃሴ አንጻር ቆሻሻው ከኮሮና ቫይረስ ባሻገር ለተዛማጅ በሽታዎች ጭምር ዋነኛ ስጋት መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ::
ተዘዋውረን የተመለከትነውን የተዝረከረከ ቆሻሻ በተመለከተ ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የጃን ሜዳ አትክልት ተራ ተቆጣጣሪዎች ሥራው በቀጥታ ከተበላሹ አትክልትና ፍራፍሬዎች ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን በመግለፅ የቆሻሻ ማስወገድን በተመለከተ ተደጋጋሚ ጥያቄ ለመስተዳደሩ ቢያቀርቡም እስካሁን ድረስ አጥጋቢ ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ይፋ አድርገዋል::
በመሆኑም ባለፉት አራትና አምስት ቀናት ብዛት ያለው ቆሻሻ በጃን ሜዳ ግቢ ውስጥ መከማቸቱን የገለፁት ሠራተኞቹ ኅብረተሰቡም ሆነ በአትክልት ሥራ የሚተዳዳረው በሺኅዎች የሚቆጠር ነጋዴ ቁርስና ምሳውን የሚመገባቸውና ተጠቅሞ የሚጥላቸው የሙዝና የአቡካዶ ልጣጮች እንዲሁም የተለያዮ ተረፈ ምርቶች አንድ ላይ ተዳምረው በየቦታው መውደቃቸው በአጭር ጊዜ አካባቢውን የቆሻሻ ማዕከል እያደረገው መሆኑን ይናገራሉ::
“ጃን ሜዳ በርካታ ተስፈኛ ወጣት አትሌቶችን ጨምሮ ብዙ ወጣቶች ከንጋት እስከ ረፋድ የተለያዮ ስፖርቶችን የሚሠሩበት ቢሆንም አሁን ያለው መጥፎና የተበከለ አየር በየጥቂት ሜትሮች ከወዳደቀው ቆሻሻ ጋር ተዳምሮ ለስፖርተኞቹ ዕለታዊ ልምምድ እንቅፋት መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል” ያለን የ23 ዓመቱ ዮናስ ወ/ሰንበት “የታከለ ኡማ አስተዳደር በጃን ሜዳ ውስጥ የሚታየውን የተጠጋጋ ግብይትና ሽያጭ በተመለከተ በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃ ካልወሰደ በስተቀር ስፍራው የቫይረሱ መተላለፊያ ዋነኛ አማራጭ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም” ሲል ስጋቱን ይፋ አድርጓል::
የጃን ሜዳው አትክልት ተራ ግንባታ ገና ሳይጠናቀቅ በተዝረከረከ አሠራር የጀመረ በመሆኑ ነጋዴዎች ያለ ምንም መከለያ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ፀሐይ እና ብርድ እየያስመቱ ሲሸጡ ተመልክተናል:: አካላዊ ንክኪና የተጨናነቀ ግብይት በሚስተዋልበት ቦታ ድንገተኛ ዝናብ ቢደርስ እንኳን ነገዴዎቹም ሆነ ገበያተኛው ኅብረተሰብ የሚጠለልበት ቦታ የለም::
በርግጥ ተዘዋውረን እንደቸመለከትነው በእንጨት የቆሙና የቆሮቆሮ ጣራ ያላቸው የመሸጫ ቦታዎች መደደውን እየተሠሩ ቢሆንም እስካሁን ድረስ አልተጠናቀቁም:: ግንባታው ቢጠናቀቅም የርቀቱ እና ቆሻሻ የማስወገዱ ጉዳይ በፍጥነት ካልታሰበበት ጃን ሜዳ የሰሞነኛው ኮሮና ቫይረስ መናኸሪያ ከመሆን እንደማይድን ነዋሪዎች ፍርኃታቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው::