ሁለት የደ/ፍሪካ ዜጋ የሆኑ ጥንዶች በህይወታቸው ታላቅ ቦታ የሚሰጡት የጋብቻ እለታቸውን ሰሞኑን ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ለመጋራት ቢወጥኑም ደስታቸውን፣ ብዙም ሳያጣጥሙ ሙሽሮቹም፣ ሚዜዎቹም፣ ወል አፈራራሚውም፣ የቅርብ ዘመዶቻቸውም ተጠራርገው ለእስራት ተዳርገዋል።
የደቡብ አፍሪካ መንግስት የሳንባ ቆልፍ (ኮሮና ቫይረስ) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት ሲል ሰሞኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ አገሪቱ ቢደነግግም የኳዙሉ ናታል ግዛት ነዋሪዎች የሆኑት ሙሽሪት እና ሙሽራው በፍቅር አለማቸው ሲመኙት የነበረው የሰርግ እለታቸውን ለማብሰር እና ጋብቻውንም በቃለ እግዚአብሔር ለማጽናት ሰሞኑን መጠነኛ ዝግጅት ብጤ አዘጋጅተው ነበር።
ይሁን እና የሰርጉ ስነ ስርአት ሊከናወን መሆኑ መረጃ የደረረሰው የክልሉ ፓሊስ ከተባለው ስፍራ ሲደርስ ሰርገኞች በአገሪቱ የታወጀው የከቤት ያለ መውጣት እና ተራ ርቆ የመቀመጥ መመሪያን ወደ ጎን ትተው፣ ሊያፈራርሟቸው የነበሩ ሰባኪን ጨምሮ ወደ ሃምሳ የሚቆጠሩ ታዳሚዎች ጋር ደስታቸውን ሊቀጩ ሲያኮበኩቡ የደረሰው ጋሼ ፖሊሱ ሙሹሮችን እንደ ወትሮው “ይዘት በረረ፣ ይዟት በረረ…” እየተጨፈረ ባሊሞዜን፣ ማርሴዲስ፣ ቴስላ… ወዘተ መኪናዎች እንዲደላቀቁ አልፈቀደም።
ይልቁንም ሙሽሪት እና ሙሽራውን ተጠርጣሪ ወንጀለኞች በማለት ወንጀለኞችን ሁሌ ወደ ጣቢያ በሚያጓጉዝበት ባለሽቦ መጋረጃ የፖሊስ መኪናው ውስጥ አጭቆ ወስዷቸዋል። በእለቱ በሰርጉ ላይ በታደሙት በሁሉም ግለሰቦች ላይም ባለፈው ስኞ ህግን የመተላለፍ ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።
ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ በላይ ዜጎቿ በወረርሽኙ የተጠቁባት፣ ከአስራ አንድ በላይ ዜጎቿ በሳምባ ቆልፍ ወረርሽኙ የተነጠቀችው ደ/አፍሪካ ለሶስት ሳምንታት የዘለቀ ከመሰረታዊ እና ወሳኝ ገዳይ በቀር ሲጋራ እና የአልኮል መጠጦችን የመሳሰሉ የማይሸጡበት ጠንከር ያለ የጸረ ኮሮና አስቸኳይ ህግ ካወጡ የአፍሪካ አገራት መካከል እንዷ ነች።