ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮ ቴሌኮም ለ2 ወር የሚቆይ፣ ዘወትር ከማለዳው 12 ሰዐት እስከ ቀኑ ዐሥር ሰዐት ድረስ ከፍተኛ ቅናሽ የተደረገባቸው የጥቅል አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚጀምር ገለፀ።
ከነገ ጀምሮ በተግባር ላይ የሚውለውና ለሁለት ወራት የሚቆየው “በቤትዎ ይቆዮ” የሞባይል ጥቅል አገልግሎት እንደጀመርኩ እወቁልኝ ያለው ዛሬ በሰጠው ይፋዊ የጋዜጠኞች መግለጫ ላይ ነው።
ተቋሙ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲያግዝ የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያደረጉትን ሀገር ዐቀፍ ብሔራዊ የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በ444 በሚያስተላልፈው መልዕክት አማካይነት 3 ሚሊዮን 700 ሺኅ ብር መሰብሰቡን አስተዋቋል::
ነገ ማለዳ 12 ሰዐት በሚጀምረው በ”ቤትዎ ይቆዮ” ጥቅል አገልግሎት ለድምፅ በአምስት ብር 30 ደቂቃ የሚቆይ የአገር ውስጥ ስልክ ጠሪና 20 ነፃ አጭር የጽሑፍ መልዕክት መጠቀም ይቻላል:: በቤትዎ ይቆዮ የሞባይል ኢንተርኔት በ5 ብር 100 ሜጋ ባይት የኢንተርኔት እና 20 ነፃ የሀገር ውስጥ አጭር የጽሑፍ መልዕክት እንደሚያገኝ ሓላፊዋ ገልጸዋል::