ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ኮሮናን ለመከላከል የተቋመው ግብረ ኃይል ምእመናን ቅዱስ ቁርባን እንዳይቀበሉ በማለት የወሰነውን ውሳኔ በመቃወም ፣ በልዩ ኹኔታ ፈቃድን እንዲሰጥ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ፃፉ።
ቅዱስ ፖትርያሪኩ ሚያዝያ 8 ዛሬ የተከበረው የጸሎተ ሐሙስ በዓልና ሚያዝያ 11ቀን የሚከበረው በዐለ ትንሣኤ ምዕመናን በአካል ተራርቀው በማስቀደስ መቁረብ እንዳለባቸውም በደብዳቤያቸው አሳስበዋል:: ፓትርያርኩ የጻፉትን ሙሉ ደብዳቤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል::
“ለክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የኢ/ፌ/ሪ/ ጠቅላይ ሚንስትር
“እኛ ከተከለከልነው መንፈሳዊ አገልግሎት ይልቅ የመከላከል ሥራውን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ከፍተኛ የሰው መጨናነቅን የሚያስተናግዱ ገበያዎች፤ አውራ ጎዳናውን የሞሉ የእግረኛ እንቅስቃሴዎች፣ የመጓጓዣ አገልግሎቶች ባልተገደቡበትና ባልተከለከሉበት ደረጃ ላይ እያለን ኹለት ወር ሙሉ በሐዘንና በንስሐ ሲጾሙ የቆዩ “ምእመናን ቅዱስ ቁርባን አይቀበሉ” የሚለው የብሔራዊ ግብረ ኃይል ውሳኔ ፍትሐዊነት የሌለውና ቤተ ክርስቲያኒቱን አደጋ ላይ የሚጥል ከመኾኑ በተጨማሪ በምእመናን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን በመቀስቀስ ወደ አላስፈላጊ ግጭት የሚከት ኾኖ ስላገኘነው በአስቸኳይ አዋጁ በተደነገገው የልዩ ፈቃድ ማስፈጸምያ ደንብ መሠረት ሚያዝያ 8 የሚከበረው የጸሎተ ሐሙስ በዓልና ሚያዝያ 11ቀን የሚከበረው በዐለ ትንሣኤ በሀገሪቱ ባሉ በኹሉም አድባራትና ገዳማት በዕለቱ የሚቆርቡ ምእመናን በተገኙበት ከጤና ሚንስትር የተሰጠውን የአካላዊ ርቀት መመርያ በጥንቃቄ ተግባራዊ በማድረግ በዓላቱ በሰላም ይከበሩ ዘንድ በልዩ ኹኔታ እንዲፈቀድልን ከአደራ ጭምር እንጠይቃለን ።”
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !!!
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፖትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ ሊቀ ጳጳስ
ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት