|| በተለይ ለደሴዎች || Ansoar Ahme
ስለ ደሴ ለመግለፅ የኢንሳይክሎፒዲያ አይነቱ በርካታ
ጥራዝ እንደማይበቃኝ አሰብኩና መተውን መረጥኩ።
ግን ከራስ ፀጉር ያህል ከበዛው የደሴ ጣፋጭ ምጭውት
ላይ አንዷን ዘለላ ለመምዘዝ ወደድኩ ።
ደሴ ስልጡን ከሚባሉ ቀደምት የኢትየጵያ ከተሞች
ማለትም ጅማ ጎንደር ሐረር እና አስመራን ጨምሮ አንዷ
ነች።
ደሴዎች ልዩ ናቸው ይባላል።
በተለየ የደሴ ልጆች ብቻ የሚረዱትት ግልፅ ሀገራዊ ለዛ
ያለው ቋንቋ አላቸው።
“እዝ ልዝ ምዝ” ለሌላ ቀን ይቀመጥ።
ስለ ደሴ ሲወራ በዘረኝነት ስሜት እንዳይመስል ዘረኝነትን
አያውቁትም።
ዘረኝነትን አትቅረቧት ጥንብ ናት! አሉ
የአለሙ እዝነት ትልቁ ሠው።
(ነብዩ መሐምድ ሰ ዐ ወ)
እርግጥ ነው ከአዝሃሩል ሀበሻ
ዋና መናገሻ ደሴ ተወልዶ ያደገ ደግሞ “ዘረኛ” ሰው
ማለት”ጥንብአንሳ” እንደሆነ ጠንቅቆ ይረዳዋል።
እኔ ግን ሀገር መውደድ ከኢማን ነው ያለው ነብያዊ ቃል
ነበር ኢማኔ ቢጨምር ብየ በሀገር መውደድ የመጣሁት።
ደሴ ላይ ፍቅር እና መዋደድ ህይወት እግር አውጥቶ
ሲራመድ ታየዋለህ።
በአባቶችና በእናቶች ደረጃ ደግሞ እያስለቀሰ
ያስደምመሃል። ጥልቅ ፍቅር።
እውነተኛውን የደሴ ለዛ “በተለይ”
60ቹ 70ቹ እና በከፊል 80ቹ ውስጥ የተወለዱትን ካገኘህ
ደሴን ታውቃታለህ።
እንዳሁኑ በታታ (TATA) ቅኝ ግዛት ያልገባችውን ደሴን።
TATA ታታ በሆድህ ምንድነው ስትል የሰማሁ መሰለኝ።
ሰውየው ሙሉ ጓደኞቹ አዲስ ከተሙና ከጓደኞቹ ዘግይቶ
እሱም ከተመ።
እንዴት ደሴን ለቀቅክ ቢሉት፣
በታታ ምክንያት አለ።
እንዴት?
የመንግስት ሰራተኛ ነኝ፣ ረጅም አመት አገልግየ ደሴ ከተማ
እገባለሁ ስለ፣ በዝውውር አንዴ ላስታ፣ ሌላ ጊዜ አቀስታ፣
ይባስ ብለው ደላንታ ሲያንከራትቱኝ ስራውን ለቅቄ በታታ
ተሳፍሬ መጣሁ አለ።
በርግጥ የአብዘሃኞቻችን ወላጆች አመጣጥና ሀገር በደሴ
ዙሪያ ገጠም ከተሞች በመሆኑ ታሪክ ራሱን እየደገመ
የተወለዱባትን ልጆቿን በትና በናፍቆትና በስማበለው
ትጦራለች።
ተወልዶ ያደገው በብሶት በእድገትና በስልጣኔም እየኮበለለ
ሲወጣ በሁለተኛው ከተማ ከፍ ሲል በሁለተኛው ሀገርም
አንዳንዴ ግጥጥሞሹ ሲፈጠር ጦሳና አዘዋገደል ቦርከና እና
ሀረጎ የቀሩ ያስመስሉታል።
ቀደም ብሎ በአባቶችና በእናቶች ዙሪያ የነበረውን
ማህበራዊ ትስስር እና አስተዋፅኦ ለመግለፅ የቋንቋ
ውበትና የቃላት መንጋ ቢፈጠርም አባይን በጭልፋ ይሆናል።
ትውልደ ደሴ የሆኑ
ተፈጥሯዊ አርቲ፣ እርጎለጋ፣ ጠጀሳር ፋጢማቆሪ፣ ብቅል
ሰበራ፣ ሚዜ ወጊ፣ ቦከታ፣ጅብ ወለደች፣ ቅሬ፣ በግጠቢ፣
ጋቻ፣ አባውዴ፣ ተርቲብ ወዘተ የደሴ ልጅ ካልሆነ በቀላሉ
የማይገቡ ውብና ብርቅ የደሴ ብቻ የቋንቋ ሃብቶች ናቸው።
አዲስ አበባ ውስጥ ነው! በአንድ ጥሪ አጋጣሚ
ተሰባስበናል።
በብዛት በአንድ ትውልድ ዘመን ያሉ የደሴ ወንድማማች
ልጆች ተገጣጥመዋል።
አብዘሃኛው በተቀራራቢ እድሜ ዙሪያ ያለ ስብስብ ነበርና
ከአሁኑ “ሀምና ገም” ከበዛበት ሃያት የዱሮውን መገረብ
የጋራ ሀሴት ይፈጥራል በሚል አንድ ሁለት በመባባል
ጨዋታው ጀመርነው:
* * *
* * * * * *
* መዲና ቁርስቤትን ጠርተህ የህንድ ፖስተር እና የጄኔራል
ሙዚቃ ቤትን ሬክላም አይይዞ ካላወራህ ፒያሳ ላይ ያለውን
የወጣቶች ክበብ ግሪን ኤሪያ አላውቀውም በለው።
* የይመር አፍሪካን ፍሩም ባትታደልኳ የኡመር ካፍቴሪያ
ስፔሻል ናሽፍ ካልበላህ በምግብ እጥረት ብትጠረጠር
እባክህ ሰው አትቀየም።
* ፎቶ አዲስ እጅ ስራ ተነስቶ ሳምንት ካልጠበቀ፣ አደም
ፎቶአዲስን ባየው ቁጥር ዘመድ ዘመዱ ካልመሰለው፣ ፎቶ
ጂጂን ካልተደመመበት፣ ፎቶ ስፖርትን ከየማታ ጋር
ካላስታወሳት፣ የፎቶ ወሎ ልጆች ካልተመሳሰሉበት፣ ፎቶ
ተራራን ብርቅ ካልሆነበት፣ አጂፕ ፊት ለፊት ፎቶ ብርሃንን
ካላስታወሰ እንኳን የደሴ ልጅ መታወቂያ የለውም።
* ደረቁ ድልድይ ስትለው ማስታወሱ ቀርቶ አፍንጫውን
ካልያዘ ወይም ግርር ካለው፣ ክላክስ ስታደርግለት መንገድ
ዘግቶ ከገለመጠህ የቀረው አለ።
* የጢጣውን መናፈሻና ካምፕ ስታወራው ውሃ ፋብሪካው
ሎጁ ጋር ካለህ “ሽርሽር” አታውቅም በለው።
* የሙቅቢል ወረቀት ስትለው፣
እ! ምንድን ነው? ካለህ። ለደጉ አባታችን “ሀጅ ሙቅቢል
አላህ የጀነት ያድርገውና” የሚል ዱአ አንተ አድርግ።
ከሙቅቢል በታች ጃንጥላ ከልሎ ፎቶ አስመስሎ የሚስለው
ሰአሊማ ያኔም ድብቅ ነው።
* ወሎ ባህል አምባ ላይ አዲሱን አውቆ የሚጨብጠውን
ጉማሬ ካላወቀ፣ “ቴምፖ” ስትለው ካልተደመመ፣ ባህል
አምባ ለፖለቲካ የተመላለሰ ካድሬ ነው።
* አየየየየይ! ብለህ በረጅሙ ስትተነፍስ፣ ከንፈሩን
እየመጠጠ ወልዩን ካልጠራ እመነኝ አዲሴ ብለህ ጥራው።
* የአሊ ፓስቲኒን የለሊት ድቤ ካልሰማ በሙሳፊርነትኳ
“ዴሴ” ዘልቆ አያውቅም እልሃለሁ። ወይም ከወደቀ
አይሰማም።
*የአኒስን ሻይ በበራድ ከነወከባው ስትተርክ ግርር ካለው
የዘመኑ የመንገድ ላይ የጀበና ቡና ሱሰኛ ነው፣ ልጋብዝህ
ብለህ አረጋጋው።
* ሴንትራል ቁርስቤት ፓፓየ በእንቁላል ካልጠጣ የሐረር
ቡናቤትን እንቁላል ቅቅልንም አያርፈውም።
* በበለጠችን ፓስቲኒ እጁም ከንፈሩም ካልወዛ ፈርቶ ነው
የሚረጋወ ዘይት በዘመኑ እንዳልነበር ግለፅለት።
* ሙጋድ ምድር ላይ የዳህላክ ሙዚቃ ቤት ለስላሳ ሙዚቃ
ያዳመጠ፣ ሞዛርትማ በግዱ ሲያቧርቅበት ይሰማዋል።
* ኤርትራውያን አረቦች ጉራጌዎች የከፋፋይ ፖለቲካ
መብረቅ እስከሚመታው ድረስ የአንድ ቤተሰብ አባል
መስሎ ሳይሆን ሆኖ ከኖር ውጭ ሀየማኖታዊው መከባበር
እንኳ ያስደምም የነበረባት ደሴ አትዘነጋም።
* አስር አለቃ ፋርማሲን ካስታወሰ በይመር አበባውና በአስኒ
ፋርማሲ እንዳታማው።
* ቴሌ መድረክ ላይ የጦሩን ኪነት ካላየ የአባማፍቀሬን እና
የጥምቀቱን ጨዋታ ድባብ እንዴት ትጠይቀዋለህ?
* የሸዋበሩን የኢድ ሰላትና ቁርአን ውድድር ስትተርክለት
ካላወቀው የሸህ መሐመድ ሻፊ አላሁ ወዳኢም ከነጭ
ጃንጥላው ስር ስላመለጠው የኢድና አረፋን ውበት ጭፈራ
መች ታደለውና!
* አባቱም ሆነ ዘመዱ ከአዲስ አበባ በበራሪውና በአንደኛው
አውቶብስ ከ12 ሰአት በኋላ ሲገባ በስይት ጠብቆ የደብረ
ሲናውን ሙዝ በቅርጫት ከነትርንጎው ተቀብሎ የዘመዱን
አንገት ከነላቡ ካልሳመ ሸዋ ሮቢት አድሮበት ነው።
* የፔፕሲብ እግርኳስ ክለብ፣ ተስፋየ ባልቻንና አበራ
ባንጃውን ካላወቀ የስፖርተኛው መሐመድ እንድሪስን
ጨዋታ ያለቦታው እንዳትተርክለት።
* የዘውዱ እናት፣ አቡየ ፈንታው፣ ውሾን፣ ሚሊዮንን ካላወቀ
አንድ ጡትንም አትተው የመድኃኒአለሙን በእውቀቱን፣
አክሊሉንም “እብድ” ነው ይልሃል።
ቴምፖ! * * *
* * * * * *
* አውቶብስተራ ጉቶ ስትለው፣ የዛፍ ስር ነው? ካለህ
ተበሳጭተህ ወደ ቢስ ቤት አትገስግስ፣ አብዱፋጤን
በማወቁ ኸይሩን አስብና ይቅር በለው።
* ሀጅ መሐመድ ጌታን ስታወሳ ሀጅ ይመር ዳውድ ግንብ
ላይ የተነሳሁት ፎቶ አለኝ ካለህ ለታሪክም ቢሆን
ተቀበለው።
* የወሎ ዳቦ በወተትና በማር እንደማይጠገብ ከነገረህ
አታስተባብል፣ ማባያው ከተገኝ የህብስተ መናውም የባቡ
ጥምዙ ዳቦ ሸጋ ነበር በለው።
* ከወይዘሮ ስህን እስከ ቦሩ ስንት ኪሎ ሜትር ነው ካለህ፣
ከፒያሳ እስከ መናፈሻ ሁለት ፌርማታ ነው በለው።
* ደሴ ሆስፒታል ግቢ ያሉትን ጎጆ ቤቶች መፍረሳቸውን
ከጠራልህ ፔፕሲ በላይ የኪውባዎቹ ቤት ህንፃ መሆን ቅርስ
እንደማይከበር ግለፅላቸው።
* ስሸህሱሌ የአዛን አወጣጥ ከተመሰጠ ስባህረዲን
አዛንም ስለሸህ አደም ኹጥባ አውርተህ አሰደምመው።
* ገባራላን ከነጭፈራው ያላወቀ ወደ ረመዳንን ድባብ መች
ያሳልፈሃል? የተራውሂ ሰላቱን ከነወዚፋው ከነሰለዋቱ
ካላስታወሰ ኺላፉ ከነገሰ መስጊድ ወይም ደሴ እንደገባ
አረጋግጥ።
* የማሪቱ ለገሰን መድመቂያ ዋሊያ ስትለው የትጋ ካለህ፣
በጠራራ ፀሀይ ባህሩ ቀኜ በረጅም ቁመቱ ጎብለል ጎብለል
ሲል መች አየኸውና፣ ዘመነ ባዴባዴሳ! እንዳትለው
ይቀየመሃል።
* ከሸዋበር እሰከ ቧንቧ ውሃ የውይይት ታሪክ ስታወራው
ስለመርሆ ግቢ መንገድ “ወክ” ሳሌ ካልገጠመህ ጦሳንም
ወጥቶ እንዳለጎበኘው አረጋግጥ።
* መንገድ ዳር ቆሞ የወታደር ዘማች ካልሸኘህ፣ ፒያሳ ላይ
አይፋና ኦራል ቆሞ ጥንድ ወ ፖ ካላየህ አብዮቱ ሲያብጥም
የለህ፣ ሲፈነዳም የለህ፣ ሲሟሽሽም የለህ በቃ መጤ ነህ።
* ወላጆችህ አኢሴማ አኢወማ በማለት አዛ ካልተደረጉ፣
አብዮት አደባባዩንም የሰልፍ ረገጣውንም አታውቀውም።
* በናቄ ሳይክል ሸርፍ ተራን ከፍየል ጋር እየጦወፈ
ካላንከራከሰ እንኳን ጆተኒ የሽቦ መኪናም አልነዳ።
* በቮልስ ዋገን እና ቤቢ ፊያት መኪና መንጃፈቃድ ላውጣት
ግራ ታፋ ቀኝ ታፋ ካላለ መንጃ ፈቃዱ እቤቱ ድረስ
የመጣለት ጉቦኛ ነው አላልኩም።
* የድሮ የግሩፕ ፀብ አራዳና ሮቢት ስትለው አገር ግዛትን
ካልጨመረልህ እንኳን ጩቤ ከያዙት ከሸሹትም አይደለም።
* ዳውዶ መስጊድ እና ቅዳሜ ገበያ ት/ ቤት ቢገጣጠሙ
ሰፊ ናቸው ካለህ የገብሬሉን ጫካ በመመንጠሩ አከሳው
እንጂ ይበልጣል በላቸው።
* ስለ ሮቢት ገበያ ስታወራው በገበያው አባጣ ጎርባጣነት
ሳትገረም የአራዳን ገበያ የዳስ ሰንሰለት በምጥን ጪስ
ታውደህ ካልዞርከው በደሴያዊነትህ አጉድለሃል።
* የኩራዝን መደብር ከጀምስቦንድ ጋር ስታጎራብት
የድሮውን ወሎ ሻይ ቤት ከነ እርጎው ካልተረከልህ
የአላሙዲንን ህንፃ ከፍታ እንዲቆጥር ፍቀድለት።
* መሰናክል ማለትነን ትቶ ቲቲአይ ካለህ ግዴለህም
ትልቁንም ባህርዛፍ የዘመዱ ያህል ያውቀዋል።
* የጦሳ ሬድዮ ጣቢያን ትምህርት ስርጭት ስትተርክ አበራ
ታየ አለሙ ካለህ ክላሲካሉም ይሰመሃል ማለት ነው።
* ዲቢጅን ስት አይጠየፍ፣ አውራ ጎዳና ስትል አቡኑ ግቢ፣
መንበረ ፀሀይ ስትል ሸህ ሁሌን ጅሩ ቢለን፣ ቀጋው ስትል
አልፎህ ሙሽራው ድንጋይ ካለህ “ዴግ በጨዋታ
ተጣግበሀልል”።
* * * * * *
* ዲቢጅን ስት አይጠየፍ፣ አውራ ጎዳና ስትል አቡኑ ግቢ፣
መንበረ ፀሀይ ስትል ሸህ ሁሌን ጅሩ ቢለን፣ ቀጋው ስትል
አልፎህ ሙሽራው ድንጋይ ካለህ “ዴግ ተሟጥለሀል”።
በትውስታ ቅኝት ደሴን ማካለሉ የአገር ልጅ ፍቅርና በንፁህ
ፍቅር መሰባሰብ ያለውን ልማታዊም ሆነ ቤተሰባዊነት
አብሮነትና ጥንካሬ ከመናፈቅ ነው ብንል ማሳበቅ
አይሆንም።
* ጓደኛህ እያንዳንዱን ስትጠራ በትዝታ ከነጎደብህ ለክፉ
ለደጉም ፒያሳ ላይ መልሰውና “ኦሊቬሊቬንቱራ!” በለው።
ምን ማለት ነው ካለህ!
አዛን አለ! ሰላታችንን እንስገድ ብለህ ቀልብ እንዳያገኝህ
ቀስ ብለህ ሂድ።
ለምን?
የደሴ ነገር የጨው ውሃ ማለት ነው።
እንዴት?
በጠጣኸው ቁጥር ጥሙ የሚጨምር።
በቀጣዩ ሙዚቃ ወደ ዋናው ስቱዲዮ ልመልሳችሁ።
ስለነበረን ጥሩ ቆይታ አመሰግናለሁ።
* * * ናፍቆት ያብዛብን!
ኧረ ደሴ ደሴ ያላየ ያየሽለት
ቁሞ ይህድንጂ ልቡንስ እንጃለት !
ኧረ እንጃለት!
እህህ ከነክንብንቧ ሳያት አረብ ገንዳ
እከተላት ጀመር አራዳ ላራዳ።
THE END