ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ባምብል ወረዳ ሦስት ሰዎች በአንበሳ ተበልተው ሕይወታቸው ማለፉን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል።
አንበሳ በአካባቢው ነዋሪ ላይ ከሞት ባሻገር የመቁሰል አደጋ በሰዎች ላይ እያደረሰ ይገኛል ተብሏል። በክልሉ “አንበሳ” ተብሎ በሚጠራው ጫካ ውስጥ የሚኖሩ አንበሶች መሀል በአንዱ አንበሳ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረሱት ትንኮሳ ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሉት የክልሉ ኮሚኒዮኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ መለሰ በየነ፤ በሰዎች ላይ ጥቃት እያደረሰች የነበረው የአንበሳ ደቦል በሰዎች መሸጡንም መረጃው አለን ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ የእንስሳት ጫካዎች ጥበቃ ስለማይደረግላቸው በተለያዮ ጊዜያት በአካባቢው ነዋሪዎችና የቤት እንስሳት ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው።
ሚያዚያ 6 ቀን 2012 ዓ.ም “ሸንግላ” ቀበሌ ከምሽቱ ሁለት ሰዐት ላይ በእርሻ ሥራ የተሠማራ አንድ ሰው በአንበሳ ተበልቶ ሕይወቱ አልፏል።
አንበሳው በተጨማሪም ግምታቸው 10 ሺኅ ብር የሚሆኑ የቤት እንስሳት ላይ ጉዳት አድርሷል። በአጠቃላይ በአንድ ወር ውስጥ በጉልማና ሸንግላ ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ ሦስት ሰዎች በአንበሳ ተበልተዋል።