ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ወቅዳሜ ዕለት ለማክፈል (የፋሲካ በዓል ዋዜማን ለማክበር) ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የሄዱ ሠባት የአዳማ ወጣቶች ሞተው መገኘታቸው ተነገረ።
በምሥራቅ ሸዋ ዞን የአዳማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ተስፋዬ ኢታና እንደተናገሩት ሠባቱ ወጣቶች (ሥድሥት ሴትና አንድ ወንድ) የቤተ ክርስቲያኒቷ መዘምራን ሲሆኑ በዓሉን በቅዳሴና ጸሎት ለማክበር ነበር ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን የተጓዙት።
እንደ አገልጋይነታቸውም ከሌሊቱ ስምንት ሰዐት ላይ በአንድ አነስተኛ ክፍል ውስጥ በመግባት መተኛታቸውን ተከትሎ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ከአንድ ሰዐት በኋላ ስፍራው ሢደርስ ስድስቱ ሴቶች ሞተው መገኘታቸውንና አንድ ወንድ ወንድ መዘምራን ደግሞ ፤ ሐኪም ቤት ከተወሰደ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን አስታውቋል።
የመዘምራኑን ሞት ምክንያት ለማጣራት አስከሬናቸው አዲስ አበባ የሚገኘው ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል መላኩን የገለፁት ኮማንደር ተስፋዬ ወጣቶቹ የተኙበት ክፍል ጀኔረተር የሚቀመጥበት ክፍል ከመሆኑ ባሻገር በዕለቱ ዝናብ እየዘነበ በመሆኑ ክፍሉን ዘግተውት እንደነበርም አብራርተዋል።