ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኮቪድ 19 ቫይረስ ሥርጭትን ለመቆጣጣር በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ምክንያት በማድረግ የሰዎች ሕጋዊ መብቶች መጣስ የለባቸውም ሲል የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን አስጠነቀቀ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸት ገብሬ፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች በፀጥታ ኃይል አባላት ጥቃት ደረሰብን የሚሉ ሰዎች እየተሰሙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በፍጥነት እንዲቆምና የፀጥታ ኃይሎች ሕግን ተንተርሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያስፈጽሙ ጠይቀዋል::
ሰሞኑን በተለያዮ ማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ በፖሊስ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው የገለፁ ሁለት ግለሰቦች ጉዳዩን ከማጉላታቸው ባሻገር የመብቶች ጥሰትና አቤቱታ የማቅረቢያ መንገድ አለመኖሩ ጉዳዮን የበለጠ ሳቢ አድርጎታል ነው የተባለው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በፀጥታ ኃይሎች በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ከተከሰቱ ክትትሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በእንዲህ ያለ ሀገራዊ የችግር ወቅት በሁሉም ረገድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል::
የሰብኣዊ መብቶች መከበር አስፈላጊነትና ከግል ተሽከርካሪዎች የእንቅስቃሴ ገደብ ጋር በተገናኘ በመዘዋወር ነፃነትና በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የሚጣል ማናቸውም አይነት ገደብ፣ የሰብዐዊ መብቶች መርህን የተከተለ መሆን ይገባቸዋል ያለው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥት የሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ በሕገ መንግሥቱና በዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብት ግዴታዎችና መርሆች መሰረት የተመራ ሊሆን እንደሚገባም አስምሮበታል።