ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በተለምዶ አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሸራ ወጥሮ ሕገ ወጥ- ቤት በመሥራት 20 ሰዎችን በቤቱ ሰብስቦ ሺሻ ሲያስጨስ የነበረ ግለሰብ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
መንግሥት ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማናቸውም ቦታ የሺሻ ማስጨስና የጫት ማስቃም አገልግሎት መስጠትን አጥብቆ ይከለክላል፡፡
የአዋጁን ክልከላ በመጣስ ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋት ምክንያት የሚሆን ድርጊት ሲፈፅም እና ሲያስፈፅም የተያዘው ይህ ግለሰብ ፤ በቤቱ ከ30 በላይ ከሚሆኑ የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎች ጋር እጅ ከፍንጅ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት ነው ተብሏል፡፡
በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ጎማ ተራ ተብሎ በሚጠራው ስፍራም በተለያዩ ሁለት ቦታዎች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሺሻ ሲያስጨሱ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል:: የመርካቶ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ቡድን ሓላፊ ምክትል ኢንስፔክተር እሱባለው ጌትነት በሁለቱ መኖሪያ ቤቶች 15 ሰዎች ሺሻ ሲያጨሱ መገኘታቸውንና 66 የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎች መያዛቸውን አረጋግጠዋል፡፡