ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ሥርጭት ምክንያት ዓለም መወጠሯን ተከትሎ ሌሎች ጉዳዮች ትኩረት እንዲያጡ አስገድዷል መባሉ ተሰማ።
ይህን ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዓለማችን የረሃብ ወረርሽኝ ያጋጥማታል ሲል ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ድርጅቱ በዚህ ዓመት የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ሰዎች በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችልም ተናግሯል።
በፈረንጆቹ 2019 በመላው ዓለም አስቸኳይ የምግብ እርዳት ያስፈልጋቸው የነበሩ ሰዎች ቁጥር 135 ሚሊዮን እንደነበር ያስታወሰው ተቋሙ ፤ በያዝነው የፈረንጆቹ 2020 ግን በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ መደረጉን ተከትሎ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 265 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል ሲል ግምቱን አስቀምጧል።
ከዚህ የተነሳ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በፈረንጆቹ 2020 በከፍተኛ ደረጃ በምግብ እጥረት ሳቢያ ረሃብ ሊያጋጥማቸው ይችላሉ ያላቸውን አምስት የዓለማችን አገራትን ይፋ አድርጓል። በልየታው የመን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዙዌላ እና ኢትዮጵያ ቀዳሚዎቹ ሀገራት ሆነዋል::
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር 112.1 ሚሊዮን መሆኑን ያሳያል:: ከጠቅላላው ሕዝብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሏል። የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶች እና የምግብ ዋጋ መናር የአስቸኳይ ምግብ ፈላጊዎች ቁጥር በእጅጉ እንዲጨምር ማድረጉን ዓለም ዐቀፉ የምግብ ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።