ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢየለማ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችትን ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል የተፈጥሮ ጋዝ የንግድ ስምምነት መፈረሙን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተጠቀሰው አካባቢ 8 ትሪሊየን ጫማ የሚገመት የተፈጥሮ ጋዝና መጠኑ እየተለየ ያለ ፈሳሽ ነዳጅ በመገኘቱ፤ ወደ ልማት እንዲገባ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል። በስፍራው የሚገኙትን ካሉብ እና ሂላላ እንዲሁም ሽላቦ የተባሉ የተፈጥሮ ጋዝ መስኮችን ለማልማት፤ ፖሊ ጂ ሲ ኤል ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ከተባለው የቻይና ኩባንያ ጋር የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ ስምምነት በዛሬው ዕለት እውን ሆኗል።
ስምምነቱ የተፈጥሮ ጋዝ ልማቱ በተካሄደባቸው የካሉብና ሂላላ እንዲሁም ሽላቦ የተፈጥሮ ጋዝ መስኮች ላይ የለማውን ክምችት በቧንቧ መስመር በማስተላለፍ ለሀገር ውስጥና ለዓለም ዐቀፍ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ነው። በቀን 190 ሚሊየን ኪዮብ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ በሀገር ውስጥ ለሚገነባ የማዳበሪያ ፋብሪካና ለሌሎች የሀገር ውስጥ ፍላጎቶች እየታየ አቅርቦቱ የሚወሰን ሲሆን፤ ወደ ውጭ የሚላከው የተፈጥሮ ጋዝ በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በሚዘረጋው የቧንቧ መስመር፣ ጅቡቲ ወደብ ላይ በሚገነባው ወደ ፈሳሽ መቀየሪያ የተፈጥሮ ጋዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የሚቀርብ እንደህነም ተገልጿል።
ይህም በቀን 215 ሚሊየን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ፈሳሽ ጋዝ በመቀየር በዓመት 1 ነጥብ 5 ሜትሪክ ቶን ፈሳሽ ጋዝ ማቅረብ ያስችላል ተብሏል።
በዚህ ፕሮጀክት ሌሎች ግኝቶችን ሳይጨምር በሚቀጥሉት 20 ዓመታት 6 ቢሊየን ዶላር ማግኘት እንደሚያስችል በጥናት መረጋገጡንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።